ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አጓጊነትን እና ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስመለከተን የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን አጠናቋል፡፡ በ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ምን ዓይነት ውጤቶችን እንደምንመለከት መገመት ይቸግራል፡፡
ፕሪምየር ሊጉ የ2025/26 ውድድሩን ከመጀመሩ በፊት ክለቦች ለበርካታ ዝውውሮች በርካታ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰዋል፡፡ በተለይ የአምናው ሻምፒዮን ሊቨርፑል ብዙ ከዋክብትን ወደ አንፊልድ አስኮብልሏል፡፡
በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የትኞቹ ክለቦች እና የትኞቹ ተጨዋቾች መጥፎ ዝውውሮችን እንዳካሄዱ ዘገባዎች እየወጡ ነው፡፡ ዘገባዎቹ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 11 ጨዋታዎችን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡
ዘ አትሌቲክስ በሠራው ዘገባ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 20 ክለቦች ወኪሎችን በምንጭነት ተጠቅሟዋል።
እነዚሁ ወኪሎች በሰጡት ሁለት-ሁለት ድምጽ መሠረት የማንቸስተር ዩናይትዱ ቤንጃሚን ሸሽኮ፣ ከብሬንትፎርድ ኒውካስትልን የተቀላቀለው ዮሃኔ ዊሳ እና ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ቼልሲን የተቀላቀለው ጃሚ ጊተንስ የዓመቱ ያልተሳኩ ዝውውሮች ወይም ፈራሚዎች ተብለዋል።
በሌሎች የተለያዩ ዘገባዎች ደግሞ ተጨዋቾች በወጣባቸው የገንዘብ መጠን፣ በአዲሱ ክለባቸው በፈጠሩት ተጽዕኖ እና ተጠብቆባቸው ከነበረው እንቅስቃሴ አንጻር ተመዝነው ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ፈራሚዎች የተባሉ ተጨዋቾች አሉ፡፡
ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የተዘዋወረው ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምርጡ ፈራሚ ተብሏል፡፡
ዶናሩማ ከበርንሌይ ተዛውሮ ኢትሃድ የደረሰውን ጄምስ ትራፎርድ ተክቶ የሲቲን የግብ ክልል መጠበቅ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግልጋሎቱ ከአጥቂው አርሊንግ ሃላንድ የማይተናነስ ነው ተብሎለታል፡፡
የ18 ዓመቱ ብራዚላዊው ኤስቲቫኦ ለቼልሲዎች ጥሩ የማጥቃት አማራጮችን በመፍጠሩ ሌላኛው ምርጥ ፈራሚ የተባለ ሲኾን በውሰት ውል ከማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን የተቀላቀለው እንግሊዛዊው ጃክ ግሪሊሽም ሌላኛው ምርጡ የፕሪምየር ሊጉ ፈራሚ ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡
የማንቸስተር ዩናይትዱ ብሪያን ምቤሞም ለክለቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ጥሩ ዝውውሮች ውስጥ እንዲጠቀስ አድርጎታል።
ስውዲናዊው አሌክሳንደር ኢሳቅ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድ ፈራሚ ኾኖ ከኒውካስል ወደ ሊቨርፑል ማምራቱ ይታወሳል፡፡ በሻምፒዮኖቹ ቤት ለዳግም ሻምፒዮናነት ታጭቶ አንፊልድ የደረሰው ኢሳቅ በሊቨርፑል መለያ አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ ምንም ግብ ሳያስቆጥር አንድ ለግብ የሚኾን ኳስ ብቻ አቀብሏል፡፡ በዚህም የፕሪምየር ሊጉ ቁጥር አንድ መጥፎ ፈራሚ በመባል ላይ ይገኛል፡፡
በሁለተኛነት መጥፎ የኾነ ዝውውር የተባለውም የሊቨርፑሉ ፍሎሪያን ዊርትዝ ነው፡፡ በባየር ሊቨርኩሰን ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ ወደ ቀዮቹ ቤት ያመራው ጀርመናዊው ዊርትዝ በቀዮቹ መለያ ምንም መፍጠር ያልቻለ ተጨዋች ኾኗል፡፡
ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ኖቲንግሃም ፎረስት አቅንቶ በኑኖ ስፒሪቶ ሳንቶ ሥር ድንቅ አቋሙን አሳይቶ የነበረው አንቶኒ ኤላንጋ ወደ ኒውካስል ከተዛወረ በኋላ በተጠበቀው ልክ መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡
በ55 ሚሊዮን ዩሮ ኒውካስልን የተቀላቀለው ስዊድናዊው ኤላንጋ እንደ ሀገሩ ልጅ ኢሳቅ ሁሉ እሱም በአዲሱ ክለቡ ውጤታማ መኾን አልቻለም። በዚህም ምክንያት ሦስተኛው መጥፎ ፈራሚ ተብሎ ተፈርጇል፡፡
ጂን ክሌይር ቶዲቦ ከኒስ ወደ ዌስትሃም፣ ሊያም ዴላፕ ከኢፕሲዊች ታውን ወደ ቼልሲ፣ ሚሎስ ኪርኬዝ ከበርንማውዝ ወደ ሊቨርፑል፣ ዣቪ ሲሞንስ ከፒኤስጂ ወደ ቶተንሃም፣ ቤንጃሚን ሴስኮ ከአርቢ ሌብዚዥ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ጃሚ ጊተንስ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ወደ ቼልሲ፣ ማድስ ሄርማንሰን (ግብ ጠባቂ) ከሌስተር ሲቲ ወደ ዌስትሃም ያደረጓቸው ዝውውሮች ከአራተኛ እስከ 10ኛ ደረጃን የያዙ በእስካሁን ባደረጉት የየክለቦቻቸው እንቅስቃሴ ያልተሳኩ ዝውውሮች ተብለዋል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መጥፎም ይሁን ምርጥ የተባሉት ዝውውሮች በተለያዩ የስፖርት ተንታኞች እና ባለሙያዎች የተለያየ ደረጃ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
የእናንተስ ምርጦቹ ዝውውሮች እና ውጤታማዎቹ ዝውውሮች የትኞቹ ናቸው?
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



