በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ኮትዲቯር ከማሊ፤ ኬፕቨርዴ ከደቡብ አፍሪካ ግማሽ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ዛሬ ይጫወታሉ።

0
231

ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 40 ሺህ ተመልካቾችን በሚይዘው ዴ ላ ፓይ ስታዲየም ኮትዲቯር ከማሊ ምሽት 2 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ ይህ ለስድስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው።

ኮትዲቯር በአራቱ ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ማሊ ኮትዲቯርን አሸንፋ አታውቅም። ኮትዲቯር በአፍሪካ ዋንጫ ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ስታስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውባታል።

የማሊ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ይዞ በመቅረብ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ አድናቆት እያስቸረው ነው። ማሊ በአፍሪካ ዋንጫው እስከ አሁን ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ ነው የተቆጠረባት።

በፊፋ ወርሐዊ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ማሊ 51ኛ ናት፤ ኮትዲቯር ደግሞ 49ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ኬፕቨርዴ ከደቡብ አፍሪካ 20 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ቻርልስ ኮናን ባኒ ስታዲየም ከምሽቱ 5 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በጥሎ ማለፉ ኬፕቨርዴ ናሚቢያን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ሞሮኮን አሸንፈው ነው ለዛሬው ጨዋታ የደረሱት። ኬፕቨርዴ እና ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2013 ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ኬፕቨርዴ ደቡብ አፍሪካን ካሸነፈች በአፍሪካ ዋንጫ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ ትገባለች። የአንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ሰባተኛ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዋን የምታደርግ ይኾናል። ኬፕቨርዴን ካሸነፈች በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ታልፋለች። በፊፋ ወርሐዊ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኬፕቨርዴ 73ኛ፤ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ 66ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here