የምሽቱ ትልቅ ጨዋታ!

0
97
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አምስተኛ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት በርካታ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 5፡00 በኢምሬትስ ስታዲየም አርሰናል ከባየርን ሙኒክ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ የዕለቱ ትልቅ ጨዋታ ነው።
አርሰናል በፕሪምየር ሊጉ ቶትንሃምን፤ ባየርን ሙኒክ ደግሞ በቡንደስሊጋው ፍራይቡርግን አሸንፈው በሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ መገናኘታቸው የተሻለ ጨዋታ ለማድረግ የሚያስችል የሥነ ልቦና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል።
አርሰናል እስካሁን ያደረጋቸውን የአውሮፖ ሻምፒዮንስ ሊግ አራት ጨዋታዎችን በማሸነፍ 12 ነጥብ ሠብሥቧል።
መድፈኞቹ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንድ ጨዋታ ብቻ መኾኑ የቡድኑን ጥንካሬ ያሳያል።
አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ጨዋታውን በሜዳቸው መጫዎታቸው በበላይነት ለማጠናቀቅ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
በአርሰናል በኩል ጋብርኤል ማጋሌሽ ከማይሰለፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መኾኑ ተረጋግጧል።
ባየርን ሙኒክ በአንጻሩ በሻምፒዮንስ ሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ እና 12 ነጥብ በመሠብሠብ በደረጃ ሠንጠረዡ በቀዳሚነት ተቀምጧል።
በ2025/2026 የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋም 11 ጨዋታዎችን አድርጎ በአንድም ጨዋታ ባለመሸነፍ ጉዞ ላይ ይገኛል። ይህም የቡድኑን ጠንካሬ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
የባየርን ሙኒክ አሠልጣኝ ቪንሴንት ኮምፓኒ ለዴይሊ ሜይል ስፖርት “እስካሁን ያቀድነውን አሳክተናል። ከአርሰናል ጋር መጫወት ከባድ ቢኾንም የምንፈልገውን ለማሳካት ነው የምንጫወተው “ብለዋል።
በባየርን ሙኒክ በኩል ሉዊስ ዲያዝ በቅጣት አይሰለፍም።
ስፖርት ሞል እንዳስነበበው ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ በ14 ጨዋታዎች ተገናኝተው ባየርን በስምንት ጨዋታዎች በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ሁለቱ ቡድኖች በሦስት ጨዋታዎችም አቻ ተለያይተዋል።
አርሰናል በአንጻሩ በሦስት ጨዋታዎች ብቻ ነው ያሸነፈው።
ሁለቱ ኃያል ቡድኖች በየሀገራቸውም ኾነ በአህጉራዊ ጨዋታዎች ጠንካራ ጉዞ ላይ መኾናቸው ዛሬ የሚያደርጉትን ጨዋታ የዓለም የስፖርት ቤተሰብ በጉጉት እንዲጠብቀው አድርጎታል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here