የባከነው አልጋ ወራሽ መጨረሻ ምን ይኾን?

0
38
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብራዚላውያን ለአልጋ ወራሽነት አጩት፤ በእግር ኳስ የገነነውን ስማቸውን እንዲያስቀጥል ተስፋ ጣሉበት፤ የልጅነት ተሰጥኦውን አይተው ከአንጀታቸው ወደዱት፤ አደነቁት፤ ስሙን እያነሱ ዘመሩለት።
በዓለም ዋንጫ ቀዳሚ የኾነ ስማቸውን እንዲያስቀጥል አደራ ጣሉበት። የቀጣዩ ዘመን መሪ ነህም አሉት። ስሟን ካስጠሯት፣ በዓለም ቀዳሚ ካደረጓት ከዋክብት ተቀብሎ ቀዳሚነቷን እንዲያስጠብቅ ሾሙት።
እርሱ ግን አልጋወራሽነቱን አልቻለበትም፤ አደራውንም አልተወጣም፤ ብራዚላውያን በፈለጉት ልክ ሳያበራ ወደ መጨረሻው ቀርቧል።
እርሱ በእግር ኳስ የደነሰ፣ በእግር ኳስ እንደ አሻው የተቀናጣ ኮከብ ነው። ብራዚል በእግር ኳስ ታሪክ ካፈራቻቸው ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ነው። ብራዚል ብቻ አይደለችም ዓለም ካየቻቸው ባለ ድንቅ ተሰጥኦ ተጨዋቾች መካከል ስሙ ይጠቀሳል። በአንድ ወቅት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ቀጥሎ የሚጠራው ኮከብ እርሱ ነበር ኔማር ጁኒየር።
ሙሉ ስሙ ኔማር ዳ ሲልቫ ሳንቶስ ጁኒየር ይባላል። የተወለደው እ.አ.አ በካቲት 05/1992 በብራዚል ሞጊ ዳስ ክሩዝስ ሳኦ ፓውሎ ነው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ያለው፣ ልዩ ተሰጥኦም የተቸረው ነው።
በለጋ እድሜው በጎዳና ላይ መጫወት የጀመረው ኔማር የእግር ኳስ ጥበቡ ብዙዎችን ማስደነቅ የጀመረው ገና በልጅነት ነው።
በብራዚል የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከዋክብትን በማውጣት የሚታወቀው ሳንቶስ ይህን ባለ ድንቅ ተሰጥኦ ተመለከተው። ተመልክቶም ወደደው። ገና በ11 ዓመቱ ወደ አካዳሚው አስገባው። በጎዳና ላይ ድንቅ ተሰጥኦ የነበረው ኔማር ብቃቱ በሳይንስ ሲታገዝ የማይጨበጥ ተጨዋቾች ኾነ። በፍጥነትም የወደፊት ኮከብነቱ ጎልቶ ታየ።
ኔማር በሳንቶስ እግር ኳስ ክለብ በፍጥነት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ኾነ። ከኳስ ጋር የሚያደርጋቸው ውብ እንቅስቃሴዎች የሳንቶስ ደጋፊዎችን ልብ ያዘ። ብራዚላውያንም አዲሱ ፔሌ ተወለደ አሉ። ኔማር በሳንቶስ ከድንቅ ብቃት ጋር ዋንጫዎችን አሳካ።
ይህን ድንቅ ልጅ ያዩ የአውሮፓ ክለቦች ተረባረቡበት። አዲሱ ፔሌ ወደ ብራዚል ተገኝቷል እየተባለ የጋዜጦች ርእሰ ጉዳይ ኾነ። የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና በ2013 ከሌሎች ልቆ ኔማርን ከብራዚል ሳንቶስ አስኮበለለ።
ለወትሮው በድንቅ ብቃት የተሞላው ኔማር በባርሴሎና ከከዋክብት ጋር ተገናኘ። ዣቪ፣ ኢኔሽታ፣ ቡስኬት እና ሜሲን ከመሳሰሉ ከዋክብት ጋር የተገናኘው ኔማር ብቃቱ እጨመረ ሄደ። በባርሴሎና የሜሴ፣ ስዋሬዝ እና ኔማር (MSN) የተሰኘው ጥምረትም እስከ መመሥረት ከፍ አለ። በዚህ ጥምረት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ ሌሎች ዋንጫዎችን በላቀ ብቃት አሸነፈ።
ለእግር ኳስ የተፈጠረ የሚመስለው ኔማር የተቃራኒ ክለብ ተጨዋቾችን የሚያስጨንቅ፣ በአሻው መንገድ የሚያልፍ፣ ኳስ አመቻችቶ የሚያቀብል፣ ግብ የሚያስቆጥር፣ አጨዋወቱ ቁጭ ብድግ የሚያደርግ የሚያሳሳ ኮኮብ ኾነ። ይህ ቀጫጫ ልጅ የዓለምን እግር ኳስ ይቆጣጠራል እየተባለ ተደነቀ።
ነገር ግን ኔማር ድንቅ ተጫዋች በኾነበት ባርሴሎና ቤት ረጅም ዓመታትን አልቆየም። በ2017 የዓለምን እግር ኳስ ያስደነቀ ዝውውር አድርጎ ወደ ፈረንሳይ ፒ ኤስ ጂ አመራ። ኔማር በወቅቱ የተዘዋወረበት 200 ሚሊዮን ፓውንድ የዓለም ውዱ ዝውውር የተፈጸመበት እና እስካሁን ድረስ ለእርሱ ብቻ የተከፈ ዋጋ ነው። ይህ ውሳኔው ግን የኔማርን ኮከብነት ያደበበዘ ነበር ይባላል።
ቢቢሲ በዘገባው ኔማር ፒኤስ ጂ 13 ዋንጫዎችን እንዲያገኝ ረድቶታል። ነገር ግን እንዲያመጣ የተፈለገውን የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ማምጣት አልቻለም ይላል።
በልጅነት ጀምሮ በብራዚል ብሔራዊ ቡድን የተጠራው ኔማር ግብ ለማስቆጠር ጊዜ አልወሰደበትም ነበር የሚለው ቢቢሲ ሀገሩን ለክብር ያበቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ተጫዋች እንደነበርም ዘግቧል። በተለይ ሀገሩ ብራዚል ባዘጋጀችው የ2014 የዓለም ዋንጫ ሀገሩን ወደ ክብር የሚመራ ተጫዋች ተብሎ ነበር። ብራዚላውያንም በእርሱ ላይ ተስፋቸው ታላቅ ነበር። ግን ተስፋቸውም ምኞታቸውም ሳይሳካ ዋንጫውን አጡት።
ኔይማር የብራዚል ታላቅ ተስፋ እንደኾነ ቢታመንም እስካሁን ድረስ ወደ ዓለም ዋንጫ ስኬት አልመራቸውም ይላል ቢቢሲ። ምንም እንኳ የብራዚል የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አግቢነትን ከሕያው ኮከቡ ፔሌ ቢቀበልም ግቦቹ ግን ለብራዚል የዓለም ዋንጫን ማምጣት አልቻሉም።
ቢን ስፖርት ኔማር ብራዚላውያን የሰጡትን የአልጋ ወራሽነት ኀላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ ካደረጉት ምክንያቶች ቀዳሚው በተደጋጋሚ የሚገጥመው ጉዳት ነው ይላል። በተደጋጋሚ የሚገጥመው ጉዳት ያን የመሰለ አስደናቂ ብቃት አውጥቶ እንዳይጠቀምበት፣ የዓለም ኮከብነትን እንዳይወስድ አድርጎታል።
ኔማር የዓለምን የእግር ኳስ ዝውውር ክብረ ወሰን ሰብሮ በመፈረም የተጫወተበትን ክለብ ለቆ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያም አቅንቶ ነበር። ከፍተኛ ወጭ ወጥቶበት፣ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ኾኖ ለሳዑዲው ክለብ አል ሂላል የፈረመው ኔማር የብቃቱ ጠላት የኾነው ጉዳት ተክትሎት ብቃቱን ሳያሳይ ቀረ። ሲጫወት ለማየት የናፈቁ የአል ሂላል ደጋፊዎች እና የሳዑዲ እግር ኳስ አፍቃሪያን ኔማርን በፈለጉት ልክ ሳያዩት ቀሩ። ኔማር
ከአል ሂላል ጋር ያለውን ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ልጅነት ክለቡ ሳንቶስ ተመለሰ።
ወደ ልጅነት ክለቡ ሲመለስ ኔማር የቀደመ ብቃቱን ሊመልስ ይችላል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። የጉዳት አዙሪት ግን ኔማርን አለቀቀውምና የሳንስቶስ ደጋፊዎች ቀድሞ የሚያውቁትን ኔማር ማየት አልቻሉም።
ቢን ስፖርት የኔማር የጉዳት ፈተና ማለቂያ የሌለው ይመስላል ይላል። በርካታ ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት አልፈውታል። ክለቡ ሳንቶስም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። አሁን ላይ በብራዚል ሴሪኤ በወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛል። ታሪካዊውን ክለብ ከመውረድ ታድጎ በ2026 የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ሕልም የሰነቀው ኔማር አሁንም በጉዳት ላይ ነው።
ቢን ስፖርት የኔማር ዓላማ ግልጽ ነው፤ ሳንቶስን ከወራጅ ቀጣና ማውጣት፣ አሠልጣኝ ካርሎ አንቾሌቲን አሳምኖ ወደ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን መመለስ ነው። ነገር ግን ጉዳቶች ከሕልሙና ከዓላማው ፊት ለፊት ተደቅነዋል ይላል።
ኔማር ወደ ብራዚል ከተመለሰ በኋላ ሜዳ ላይ ጥንካሬን፣ በራስ መተማመንን እና ተፅዕኖን መፍጠርን መልሶ ለማግኘት ሞክሮ ነበር። ነገር ግን በባርሴሎና እና በፒኤስጂ የታየውን ቄንጠኛውን ኔማር መመለስ አልቻለም ይላል ቢን ስፖርት።
ጎል ዶት ኮም በዘገባው የ2026 የዓለም ዋንጫ ከመድረሱ ከወራት አስቀድሞ ኔማር ከሳንቶስ ጋር ያለው ውል ይጠናቀቃል ብሏል። ኔማር በሳንቶስ ውሉን ያራዝማል ወይስ ይለቃል የሚለውም አልተረጋገጠም። ይህም ለዓለም ዋንጫ ሕልሙ ሌላ እንቅፋት ነው።
የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ በየክለቦቻቸው ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾች በ2026 የዓለም ዋንጫ ይሳተፋሉ። ኔይማር ወደ ዓለም ዋንጫ ሊገቡ ከሚችሉ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። ዕድሉን ለማግኘት ስድስት ወራት አሉት። ብቃቱን ማሳየት አለበት። የብራዚል ሊግ ሲያልቅ የተወሰነ የእረፍት ጊዜ ይኖረዋል። ከዚያም ብቃቱን እና አካላዊ ሁኔታውን እንደገና ማሳየት አለበት ብለዋል።
ኔማር በቀሩት ወራት ብቃቱን መልሶ የብራዚልን ብሔራዊ ቡድን ይቀላቀላል ወይስ እርሱም ብራዚላውያንም በእርሱ ላይ የጣሉት ተስፋ ሳይሳካ ይቀራል? የሚለው ይጠበቃል። የባከነው አልጋ ወራሽ የእግር ኳስ ሕይወት መጨረሻ ምን ይኾን? ጊዜ መልሰ አለው።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here