ነገርን ነገር ሲያነሳው

0
35
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎አራት ግልጽ የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄዎች፣ የተበዳይነት ስሜት፣ የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በእግር ኳስ ሜዳ። ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2009፣ ተጋጣሚዎቹ ደግሞ ቼልሲ እና ባርሴሎና።
የእንግሊዙ ክለብ ደጋፊዎች በአደባባይ ተዘረፍን ብለው አሁንም ድረስ በቁጭት የሚንገበገቡበት፣ የጨዋታው ዳኛ ከጨዋታው በኋላ ለህይወታቸው በመስጋት በዙ ውጣውርድ ያሳለፉበት፤ ሰላማዊ እግር ኳስ መልኩን ቀይሮ ለስሜት ቦታውን የሰጠበት መልክ።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ቼልሲ እና ባርሴሎና የመጀመሪያውን ዙር ኑካምፕ ላይ ዜሮ ለዜሮ ተለያይተዋል። የመልሱ ጨዋታ በስታንፎርጅ ብሪጅ ቼልሲ ማሸነፍ ባርሴሎና ደግሞ ከማሸነፍ በተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ አቻ መለያየት ለፍጻሜ ያደርሰዋል።
ጨዋታው ሲጀመር የእንግሊዙ ክለብ የጋርዲዮላው ባርሴሎናን ተጭኖ መጫወት ጀመረ። ጋናዊው ማይክል ኢሴን ግብ አስቆጥሮም የቼልሲን አጀማመር አሳመረው። ጨዋታው 1ለ0 በቀጠለበት አጋጣሚ የባርሴሎናው ኤሪክ አቢዳል በካርድ ከሜዳ መውጣቱም ለቼልሲ ደጋፊዎች ሌላ መልካም አጋጣሚ ነበር።
ነገር ግን ወደ ጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተፈጠሩት ክስተቶች ለቼልሲ ደጋፊዎች የሚዋጡ አልኾኑም።
ጫና የበዛባቸው የባርሴሎና ደጋፊዎች የፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ፈጸሙ። ነገር ግን የዕለቱ ኖርዌያዊ ዳኛ ሁሉንም ጥያቄዎች አለፏቸው።
የቼልሲ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡም ዳኛው ኦቭሪቦ የቀረቡ ግልጽ አራት የፍጹም ቅጣት ጥያቄዎችን ሁሉንም ውድቅ አደረጉ። በዚህ እሳት የጎረሱ የቼልሲ ተጫዋቾችን ከአቅል ያስወጣ ክስተት ተጨመረ።
ባርሴሎና በአንድሬስ ኢኔስታ አማካኝነት ግብ አስቆጠረ። የጨዋታው ውጤት አንድ እኩል ነው፤ ይሄ ደግሞ ከሜዳው ውጭ ግብ ያገባ በሚለው ሕግ ባርሴሎናን ያሳልፋል። ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ። የቼልሲ ተጫዋቾች ራሳቸውን መቆጣጠር አልቻሉም።
ዲዴር ድሮግባ ዳኛውን ለመደባደብ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ፣ ጆዜ ቦዚንጓ ዳኛውን እስኪበቃው ሌባ እያለ አጥረገረጋቸው። ማይክል ባላክ እና ሌሎችም የኾነውን ለመቀበል ተቸገሩ።
እንደምንም ከሜዳ የወጡት ኖርዌያዊ ዳኛ በቼልሲ ደጋፊዎች የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ምክንያት ሆቴል እስከመቀየር ደርሰዋል። ዲዴር ድሮግባና ቦዚንጓ በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ቅጣት አስተናግደዋል።
ከጨዋታው 10 ዓመታት በኋላ ስለክስተቱ ለማርካ ሃሳብ የሰጡት ዳኛው ኦቭሪቦ ስህተት መፈጸማቸውን አንስተዋል። “ቀኑ በልኬ የተገኘሁበት አልነበረም በጨዋታው ስህተቶች ነበሩ ሲሉ አምነዋል።
ይህ ክስተት በቼልሲ ደጋፊዎች ዘንድ “የስታንፎርድ ብሬጅ ቅሌት” እየተባለ ይጠራል። ክስተቱ በርካታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁንም ድረስ በተለይ ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ በተገናኙ ቁጥር እንደ አዲስ ይነሳል።
ዛሬ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቼልሲ እና ባርሴሎና ይጫወታሉ። ነገርን ነገር ሲያነሳው “የስታፎርድ ብሪጅ ቅሌትን” አነሳን።
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here