ቼልሲ እና ባርሴሎናን የሚያገናኘው ጨዋታ ከምሽቱ ጨዋታዎች መካከል ትልቅ ግምት አግኝቷል።

0
35
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 36 ቡድኖችን እያሳተፈ የሚገኘው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አምስተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ በዘጠኝ ከተሞች ይካሄዳል፡፡
በተለይ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ባርሴሎናን ምሽት 5፡00 የሚገጥምበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ባርሴሎና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ፣ በሁለቱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ በመለያት፣ በአንዱ በመሸነፍ እና አምስት ንጹህ ግብ በመያዝ ሰባት ነጥብ በመሠብሠብ 11ኛ ላይ ይገኛል፡፡
ቼልሲም ከአራት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ በመለያት፣ በአንዱ በመሸነፍ እና ሦስት ንጹህ ግብ በመያዝ ሰባት ነጥብ በመሠብሠብ 12ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ17 ጨዋታዎች ተገናኝተው ባርሴሎና ስድስቱን ሲያሸንፍ ቼልሲ በአምስት ድል አድርጓል፡፡ በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ባርሴሎና በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ስምንት ጨዋታዎችን አድርጎ ቸልሲ በአምስት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው፤ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የባርሴሎና አሠልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ ለፉትቦል እስፓኞል እንዳሉት የቡድኑ ግብ አስቆጣሪ ማርከስ ራሽፎርድ ገጥሞት ከነበረው ህመም አገግሟል፡፡
ላሚን ያማልም በጥሩ ሁኔታ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አሠልጣኙ አክለውም የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ቀላል አለመኾኑን ጠቁመው ቡድኑ ከፍተኛ የራስ መተማመን አለው ብለዋል፡፡
”በጠንካራ ሥራዎቻችን እናምናለን፡፡ እናም በዛሬው ጨዋታ ሁሌም እንደምናደርገው ለማሸነፍ እንጫወታለን” ሲሉ አሠልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ ተናግረዋል።
የቸልሲ እግር ኳስ ቡድን በድረ ገጹ አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ”ባርሴሎና የማይታመን ቡድን ነው፡፡ ነገር ግን ጨዋታውን ለማሸነፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ማለታቸውን አስነብቧል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች፦
👉አያክስ ከቤኒፊካ እና
👉 ጋላታሳራይ ከዩኒየን ሴንት ጊሎስ ምሽት 2:00
👉ማንቸስተር ሲቲ ከባየር ሊቨርኩሰን
👉ማርሴይ ከኒውካስትል ዩናይትድ
👉ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከቪያሪያል እና
👉ቡዶ ጊልሜት ከጁቬንቱስ
👉ሰለላቪያ ፕራግ ከአትሌቲክ ክለብ
👉ናፖሊ ከካራባግ በተመሳሳይ ምሽት 5፡00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሻምፒዮንስ ሊጉን ባየርን ሙኒክ፣ አርሰናል እና ኢንተር ሚላን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ እየመሩት ነው።
ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ የሚይዙ ቡድኖች በቀጥታ ወደቀጣዩ ዙር ያልፋሉ፡፡ ከ9 እስከ 24 የሚያጠናቅቁት ቡድኖች ደግሞ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች እንደሚጠብቃቸው ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here