ታላቁ ሩጫ ከሩጫ ባለፈ የሀገሪቱ አንዱ መለያ ነው።

0
12
አዲስ አበባ: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 25ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ኅዳር 14/2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ሲኾን በ25ኛ ውድድሩ 55ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።
ውድድሩን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮሞሽን እና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ እንደገና አበበ (ዶ.ር) ታላቁ ሩጫ ከሩጫ ባለፈ የሀገሪቱ አንዱ መለያ መኾኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ደግሞ የውድድሩ መሥራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የማይተካ ሚና መጫወቱን እና ከፍተኛ ምሥጋና እንደሚገባው ገልጸዋል።
ሚኒስትር ድኤታው ታላቁ ሩጫ ከውድድር ባለፈ ስፖርት፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት በኩል ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድደር በተጨማሪ ታላቁ ሩጫ በበቆጂ፣ በሀዋሳ፣ በአርባ ምንጭ እና በጅማ የሚያካሂዳቸው ውድድሮች ቱሪዝሙን በማነቃቃት እና ሀገርን በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ሚና መወጣቱንም ጠቁመዋል።
የውድድሩ መሥራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ “25ኛ ዓመታችንን ማክበራችን ብቻ ዘንድሮ በርካታ ስኬቶችን ያገኘንበት ነው” ብሏል
ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር ያደረጉት ስምምነት እና የዓለም አትሌቲክስ ቅርስን መርከባቸው ልዩ ክብር እንደኾነ አስታውሷል።
ታላቁ ሩጫ ዛሬ ላለበት ከፍታ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ አካላትንም አመሥግኗል።
ውድድሩን እንደ ባለፉት 24 ዓመታት ሁሉ በስኬት እና በድምቀት ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።
ለውድድሩ ከተዘጋጁ የመሮጫ መለያዎች ውጭ ሌሎች ቲሸርቶችን አድርጎ መሮጥ እንደማይቻልም ተመላክቷል።
ታላቁ ሩጫ የኢዮቤልዩ በዓሉን በሚያከብርበት በዘንድሮው ውድድር በርካታ ታላቅ አትሌቶች በክብር እንግድነት የተጋበዙ ሲኾን ዳንኤል ኮማን፣ ሞሰስ ኪፕቶም፣ ካሊድ ካኑቺ እና መሰል አትሌቶች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ፦ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here