በሀላባ ዞን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እየተገነባ ነው።

0
102
ባሕር ዳር: 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስታዲየሙ የመጀመሪያው ዙር ግንባታው በፊፋ ባለሙያዎች ጸድቆ እውቅና ማግኘቱንም የዞኑ አሥተዳደር ገልጿል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀላባ ዞን አሥተዳዳሪ ሙህዲን ሁሴን የአካባቢው ሕዝብ ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ያለው እና ለስፖርቱ አስተዋጽኦ ያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል። በስፖርት ቱሪዝም አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ ታልሞ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ለመገንባት ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።
በዞኑ ከተማ ሀላባ ቁሊቶ የሚገነባው ዓለም አቀፍ ዘመናዊ ስታዲየም ደረጃውን ጠብቆ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የስታዲየም ችግር ይቀርፋልም ብለዋል።
በሀገራችን ከሚገነቡ የስታዲየም ግንባታዎች በተለየ መልኩ ግንባታው ከሜዳው ተጀምሮ ወደ ቀሪው ግንባታ የሚቀጥል በመኾኑ ደረጃውን የጠበቀ እና ተመራጭ እንዲኾን አድርጎታልም ነው ያሉት።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የፊፋ ባለሙያዎች መጥተው ማጽደቃቸውን በመግለጽም በቀጣይ በካፍ እውቅና እንዲኖረውም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሰው ሠራሽ ሳር የማንጠፍ ሥራው የተከናወነ ሲኾን የመሮጫ ትራክ ንጣፉንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታም የትሪቡን መቀመጫ ወንበሮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመብራት እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለመሥራት ታቅዷል ነው ያሉት።
ሙሉ በሙሉ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በ2 ቢሊዮን ብር ወጭ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ የገባው ስታዲየሙ ከግንባታ እቃዎች ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተያይዞ እጥረት እንዳያጋጥም በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here