በታሪክ ሁለተኛው ተከላካይ

0
114
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቅ ሕልም፣ ጠንካራ ሥራ እና ለሥራ የታመነ ሥነ ምግባር ለታላቁ ሽልማት አብቅቶታል። ጠንክሮ መሥራት፣ ለሥራ መታመን፣ ሥራን በጥሩ ሥነ ምግባር መጠበቅ ለስኬት እንደሚያበቃ ምሳሌ ኾኗል።
ሁሉም ሰው የራሱ የኾነ ተሰጥኦ ይኖረዋል። ተሰጥኦ ግን በጠንካራ ሥራ ካልታገዘ ብቻውን በቂ አይደለም። እርሱ የተሰጠውን በሚገባ ያወቀ፣ ከተሰጥኦው ላይ ሥራ የጨመረ፣ በሥራውም ከስኬት አደባባይ ላይ የቆመ ኮኮብ ነው።
በዚህ ዘመን ሊታዩ ከሚናፈቁ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ነው ሞሮኳዊው ኮኮብ አሽራፍ ሀኪሚ።
የዓለም የእግር ኳስ ከዋክብትን የሚመርጠው የባላንዶር ሽልማት ለእጩነት ካቀረባቸው ምርጥ አሥር ተጨዋቾች መካከል አንደኛው ነው።
በባላንዶር ሽልማት ምርጥ ተብለው ከተመረጡ 10 ተጫዋቾች መካከል ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአፍሪካ አህጉር ደግሞ ቀዳሚ በመኾን የዓመቱ ምርጥ ተጨዋቾች ተብሎ ተመርጧል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ( ካፍ) ትናንት ምሽት በሞሮኮ ራባት የአፍሪካ ምርጦችን ሸልሟል። ሞሮኳዊው ኮኮብ አሽራፍ ሀኪሚ በትውልድ ሀገሩ በተደረገው የሽልማት ሥነ ሥርዓት አሸናፊ ኾኗል።
ይህ አፍሪካዊ ኮከብ ለብዙ አፍሪካዊ ወጣቶች አርዓያ መኾን የሚችል ነው። ፉክክር በበዛበት የዓለም እግር ኳስ ተፎካክሮ ራሱን ተመራጭ ያደረገ ኮከብ ነውና። በዚህ ወቅት ሁሉም ክለቦች ቢኖረኝ ብለው የሚመኙት ኮከብ ነው።
በፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፒኤስጂ አስደናቂ ብቃት ላይ በመገኘት በዋንጫ የታጀበ ዓመትን ያሳለፈው ኮከቡ አፍሪካ የዚህ ዓመት ምርጡ አንተ ነህ ብላዋለች።
አሽራፍ ሀኪሚ እ.ኤ.አ ከ1998 ወዲህ ይህን ያደረገ የመጀመሪያው ሞሮኳዊ ተጨዋች ኾኗል። በ1998 የሀገሩ ልጅ ሙስጠፋ ሃጂ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር። ሀኪሚ ይሄን ሽልማት ያሸነፈ አምስተኛው ሞሮኳዊ ተጨዋቾች ነው።
ከግብጻዊው ኮከብ ሞሐመድ ሳላህ እና ከናይጀሪያዊው ኮከብ ቪክቶር ኦስሜህን በልጦ የዓመቱ ምርጥ የተባለው ሀኪሚ በ52 ዓመታት ውስጥ ሽልማቱን ያገኘ የመጀመሪያው ተከላካይ ነው።
በ1973 የዚያኔዋ ዛየር የአሁኗ ዶሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች የነበረው ብዋንጋ ሺመን ካሸፈነ በኋላ ሀኪሚ የመጀመሪያው ተከላካይ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል።
አሽራፍ ሀኪሚ ክለቡን እና ሀገሩን ለዓመታት ወጥ በኾነ ድንቅ ብቃት አገልግሏል። ይህም ሽልማት ለዚያ ወጥ ለኾነ ብቃት የተሰጠ ነው። ሞሮኮ በ2022ቱ የኳታሩ የዓለም ዋንጫ በድንቅ ብቃት ለግማሽ ፍጻሜ ስትደርስ የሀኪሚ ሚና ድንቅ ነበር።
ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው እስከ ግማሽ ፍጻሜው ድረስ የተጓዘችበት ድንቅ ብቃትም በአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ ያደርጋታል።
የመከላከያ ጥንካሬን ከማጥቃት ፍጥነት ጋር በማጣመር የያዘው ሀኪሚ በሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያለው ተጽዕኖ እና የመሪነት ብቃት ከአፍሪካ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንዲኾን አድርጎታል።
ትልቁን ክብር ያሳካው አሽራፍ ሀኪሚ በሽልማቱ ፊት ቆሞ “አፍሪካዊ በመኾኔ እኮራለሁ” ብሏል። ለዚህ የተከበረ ስኬት እና ሽልማት ላበቁት፣ ከልጅነቱ ጀምሮ በእርሱ ብቃት ለተማመኑ ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።
“ይህንን የተከበረ ሽልማት በማሸነፌ በእውነት ኩራት ይሰማኛል። ይህ ሽልማት ለእኔ ብቻ ሳይኾን በአፍሪካ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመኾን ለሚመኙ ጠንካራ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ ነው” ብሏል።
የሀኪሚ ብቃት እና የእግር ኳስ ስኬት ባልተመቻቸ ሜዳ ላይ ለሚጫወቱ አፍሪካውያን ታዳጊዎች ስንቅ የሚኾን ነው።
ሞሮኮ ወርልድ ኒውስ የተሰኘው ሚዲያ “ሞሮኳዊው ኮኮብ አሽራፍ ሀኪሚ የአፍሪካ ባላንዶርን አሸንፏል፤ ይህም ቁርጠኝነቱን፣ ጠንካራ ሥራውን እና ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር ያሳያል” ነው ያለው።
ሀኪሚ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ የሞሮኮ እግር ኳስ እንዲያድግ ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርቧል። ሞሮኮ አሁን ላይ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ስም እየገነባች ነው። ለዚህ ደግሞ የሀገሪቱ መንግሥት ለእግር ኳስ የሰጠው ትኩረት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የካፍ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋቾች ላይ የተገኙት የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ሞሮኮ ለእግር ኳስ መሠረተ ልማት ለሰጠችው ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።
አሁን በጉዳት ላይ የሚገኘው ሀኪሚ በአፍሪካ ዋንጫ ለሞሮኮ ሁሉንም ነገር እንደሚሰጥ ገልጿል። ከወራት በኋላ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለዋንጫ ክብር ከሚጠበቁ ሀገራት መካከል ሞሮኮ አንደኛዋ ናት።
ለዚህ ክብር ደግሞ የሀኪሚ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚኾን ይጠበቃል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here