ባሕር ዳር፡ ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረንሳዊው ዴዚሬ ዱየ በፒኤስጂ እና ፈረንሳይ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ድንቅ ብቃት እያሳየ ያለ የ20 ዓመት ታዳጊ ነው። ብልህ እና ነገሮችን በትኩረት የሚከታተል ተጨዋች ነው ይሉታል።
በቤተሰቡ ውስጥ ብቸኛው የእግር ኳስ ተጫዋች አይደለም ዴዚሬ ዱየ። ታላቅ ወንድሙ፣ አጎቱ እና የአጎቱ ልጅም አንጀራቸው በእግር ኳስ ነው። ወደ እግር ኳሱ ዓለም ሲቀላቀልም ብዙ እገዛ አድርገውለታል። አርዓያ የኾነው ግን ኔማር እንደኾነ በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።
ዴዚሬ የሀገሩ ፈረንሳይ የተለያዩ የወጣቶች ቡድን እና የኦሎምፒክ ቡድንን በመወከል ተጫውቷል። በዚህም የብር ሜዳሊያ ሽልማትን አግኝቷል። አሁን ላይ ለፒኤስጂ እየተጫወተም ይገኛል።
በአውሮፓውያኑ 2024 የፈረንሳይ ሻምፒዮን ፒኤስጂን በ50 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ገንዘብ ነው የተቀላቀለው። ቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ ሦስት ዋንጫዎችን ቡድኑ ሲያሳካም ቁልፍ ሚና ነበረው። በ61 ጨዋታዎች 16 ጎል ሲያስቆጥር ግብ የኾኑ 16 ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።
በዚሁ ዓመት በፒ ኤስ ጂ ውስጥ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው በጧት የደመቀው ኮከብ የ2025 ጎልደን ቦይ ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል።
በየዓመቱ ከ21 ዓመት በታች ለኾኑ ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋቾች የሚሰጠው ይህ ሽልማት ባለፈው ዓመት የባርሴሎና አጥቂ ላሚን ያማል ነው ያሸነፈው። ይህን ሽልማት ዱዌ ከሰሞኑ ማሸነፉ ይታወሳል።
በቀጣዩ ዘመን ሜዳ ላይ እንደሚነግሱ ከተገመቱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዱዌ ዘንድሮ በጉዳት ምክኒያት ብዙ የመጫወት ዕድል አላገኘም። ባለፈው መስከረም ለፈረንሳይ ሲጫዎት ጉዳት ገጥሞት የነበረው ፈረንሳዊ ኮከብ ድጋሜ የጡንቻ ጉዳት ላይ እንደሚገኝ የሊኩዮፕ መረጃ እማኝ ነው።
ነገር ግን ገና በ20 ዓመቱ የፒኤስጂ እና ፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ነው።
በተለይ ባለፈው ዓመት ምባፔን በሪያል ማድሪድ የተነጠቀው ፒኤስጅ ውጤታማ እንዲሆን ዱዌ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



