አራት የአፍሪካ ሀገራት ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ብርቱ ፉክክሩ ያደርጋሉ።

0
59
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ አዘጋጅ በኾኑበት የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ 48 ሀገራት ተሳታፊ ይኾኑበታል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በዘጠኝ ምድብ ተደልድለው በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተጫውተዋል።
ከየምድቡ በአንደኝነት ያጠናቀቁት ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ኮትዲቫር፣ አልጀሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና እና ሞሮኮ ለዓለም ዋንጫው አላፊ ኾነዋል፡፡
ምርጥ ሁለተኛ ኾነው የጨረሱ አራት የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የእርስ በእርስ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት በሀገረ ሞሮኮ ያደርጋሉ፡፡
ምሽት 1:00 ላይ ናይጄሪያ ከጋቦን የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል።
የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ሦስት ላይ ተደልድሎ 10 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በአራት ጨዋታዎች አሸንፎ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ እና በአንዱ ተሸንፎ 17 ነጥብ በመያዝ በምርጥ ሁለተኛነት አጠናቆ ነው ለዛሬው ጨዋታ የደረሰው፡፡
የሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የወቅቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የኾነውን ቪክቶር ኦሲምሄን የመሳሰሉ ከዋክብትን የያዘ በመኾኑ ለጨዋታው ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።
ምድብ ስድስት ላይ ተደልድላ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዋን ያደረገችው ጋቦን ደግሞ ከ10 ጨዋታዎች በስምንቱ አሸንፋለች፡፡ በአንዱ አቻ በመለያየት እና በአንዱ በመሸነፍ 25 ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን በምርጥ ሁለተኛነት አጠናቃለች፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ስምንት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማሸነፉ የቡድኑን ጠንካራነት ያመላክታል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ናይጄሪያ እና ጋቦን በዘጠኝ ጨዋታዎች ተገናኝተው ናይጄሪያ በአምስቱ አሸንፋ እና በሦሥቱ አቻ በመለያየት ቀዳሚ ናት፡፡ ጋቦን ናይጀሪያን ድል የነሳችው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ካሜሮን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሽት 4:00 ላይ በሞሮኮ ይጫወታሉ። በማጣሪያው ምድብ አራት ላይ ተደልድላ ጨዋታዋን ያደረገችው ካሜሮን ከ10 የምድብ ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፋለች፡፡
በአራቱ ደግሞ አቻ በመለያየት እና በአንዱ በመሸነፍ 19 ነጥብ በመያዝ ምርጥ ሁለተኛ ኾና ነው ለዛሬው ፍልሚያ የደረሰችው፡፡
አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የኾነችው ካሜሮን ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ከባድ ፈተና ይጠብቃታል ነው የተባለው። ምድብ ሁለት ላይ 10 ጨዋታዎችን ያደረገችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሰባት ጨዋታዎች አሸንፋ፣ በአንዱ አቻ ተለያይታ እና በሁለቱ ተረትታ 22 ነጥብ በመሰብሰብ ነው ለጨዋታው የቀረበችው፡፡
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምድቡን በ24 ነጥብ በመምራት ዓለም ዋንጫን ከተቀላቀለችው ሴኔጋል ሁለት ነጥብ ዝቅ ብላ ማጠናቀቋ የስብስቡን ኃያልነት ያመላክታል፡፡ እናም ጨዋታውን ከባድ ያደርገዋል ፡፡
ስፖርቲንግ ኒውስን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here