የጠንክሮ መሥራት ምሳሌ…

0
58
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ወቅት የሚበላው ምግብ አጥቶ የተቸገረ ቢሆንም አሁን ላይ የሃብት መጠኑ 1ቢሊየን ዶላር ተሻግሯል። እንደ ሌሎች እኩዮች በልጅነት ዕድሜው ኳስ ለመጫወት ፍላጎት ቢኖረውም የመጫዋቻ ጫማ ግን ማግኘት አልቻለም።
ነገን የተሻለ ለማድረግ እሩቅ አልሞ ካሰበበት በላይ ገዝፎ የተቀመጠ፤ ጠንክሮ መሥራት ካሰቡበት መድረስ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ስኬታማ ተጫዋች ነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶስ ሳንትስ አቪየሮ።
ከዝቅተኛ ነዋሪ ቤተሰቦቹ በአውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት የካቲት 5/1985 ከፖርቹጋሏ ዋና ከተማ ሊዝበን በ965 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ገጠራማዋ ደሴት ማዴራ ነው የተወለደው።
ወላጅ አባቱ ከአውሮፓውያኑ 1981 እስከ 1989 ድረስ የአሜሪካ 40ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ሮናልድ ዊልሰን ሬገን አድናቂ ስለነበሩ የልጃቸውን መጠሪያ ስም ሮናልዶ ሊሉት ችለዋል።
የወላጆቹ አራተኛ ልጅ እንደኾነ የሚነገርለት ክርስቲያኖ ሮኖልዶ በ15 ዓመቱ ልቡ ላይ ያጋጠመው ሕመም እግር ኳስን እስከ ወዲያኛው ድረስ እንዳይጫወት የሚያደርግ ፈተና አጋጥሞት ነበር።
የተሳካ ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላም በስፖርቲንግ ሊዝበን ያሳየው ድንቅ ብቃት በበርካታ የአውሮፓ ክለቦች እንዲፈለግ አድርጎታል።
በአውሮፓውያኑ 2003 ማንችስተር ዮናይትድ 12 ሚሊዮን ፓውንድ ለስፖርቲንግ ሊዝበን በመክፈል ተጫዋቹን የግሉ አደረገው።
በ2007/08 የውድድር ዘመን ማንችስተር ዩናይትድ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ ሮናልዶ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር።
በሁሉም ዉድድሮች ላይም 42 ግቦችን በማስቆጠር በ22 ዓመት ዕድሜው የባላንዶር ተሸላሚ በመኾን ምርጥ ተጫዋች መኾኑን አስመስክሯል።
የማዴራው ፈርጥ በማንችስተር ዩናይትድ በነበረው ቆይታ ሦሥት የእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ፣ አንድ የአውሮፓ ቻምቺዮንስ ሊግ፣ አንድ የፊፋ የክለብ ዋንጫ፣ አንድ የኤፍ ኤ ካፕ፣ ሁለት የእንግሊዝ ካፕ እና አንድ የኮሚኒቲ ሽልድ ዋንጫዎች አሳክቷል።
ፖርቹጋላዊውን ጥበበኛ በጥብቅ ሲፈልጉት የነበሩት ሪያል ማድሪድ በ2009 በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን በኾነ ወጭ 80 ሚሊዮን ፓውንድ ለማንችስተር ዩናይትድ በመክፈል ወደ ሳንቲያጎ ቤርናባው አዛወሩት።
ተጫዋቹ በሎስብላንኮዎቹ ቤት በነበረው ቆይታ የዓለም ኮከብ ተጫዋች መኾኑን ሜዳው ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ አስመስክሯል።
በመጀመሪያዉ ዓመት የሪያል ማድሪድ ቆይታው 32 ግቦችን አስቆጠሯል። በ2010/11 የውድድር ዘመን 40 ግቦችን በላሊጋዉ በማስቆጠር የላሊጋው ኮከብ ጎብ አስቆጣሪ ነበር። በ2012 የውድድር ዓመት 46 ግቦችን በማስቆጠር የላሊጋውን ዋንጫ ከሪያል ማድሪድ ጋር አንስቷል።
ከ2009 እስከ 2018 ባሉት ጊዜያት ሪያል ማድሪድ አራት የአዉሮፓ ቻምዮንስ ሊግ፣ ሁለት የላሊጋው ዋንጫ ጨምሮ 15 ዋንጫዎችን እንዲያነሳ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል። የሪያል ማድሪድ ቆይታው በዋንጫ ሲታጀብ ለአራት ጊዜ የባላንዶር ሽልማትን ወስዷል።
ለስፔኑ ክለብ በተሰለፈባቸው 438 ጨዋታዎች ላይ 450 ግቦችን በማስቆጠር የምንግዜም የሪያል ማድሪድ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመኾን የክለቡ ታሪካዊው ተጫዋች ነው ሮናልዶ።
ሮናልዶ በእግር ኳስ ሕይወቱ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ቢኾንም በ2017/18 የውድድር ዘመን በአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ በጁቬንቱሰ ግብ ጠባቂ በጂያንሉጂ ቡፎን ላይ በመቀስ ምት ያስቆጠራት ግሩም ግብ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በልዩነት ትታወሳለች
ይችን ግብ ተጫዋቹ ሲያስቆጥር የጁቬንቱስ ክለብ ደጋፊዎች ሳይቀር ከመቀመጫቸው ተነስተው በማጨብጨብ ያላቸውን ክብር ገልጸውለታል።
የክለቡ ደጋፊዎች ያሳዩት ክብርም የሮናልዶን ልብ አሸፈተው።በነጩ መለያ የደመቀበትን የዘጠኝ ዓመታት ቆይታ አጠናቅቆ በሐምሌ 2018 የጣሊያኑ ክለብ ጀቬንቱስ ለሪያል ማድሪድ 105 ሚሊዮን ፓዉንድ በመክፈል ለአራት ዓመታት የሚያቆየውን ኮንትራት እንዲፈርም አድርጎታል።
በጣሊያን በነበረው የሦሥት ዓመታት ቆይታ ሁለት የጣሊያን ሴሪኤ፣ አንድ የኮፓ ጣሊያን፣ ሁለት የጣሊያን ሱፐር ካፕ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።
ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ሜዳ ላይ የሚያሳየው ብቃት እንደ ወይን እየጣፈጠ የቀጠለው ሮናልዶ የቀድሞ ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ያቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ በመቀበል እ.ኤ.አ ነሐሴ 2021 ወደ ኦልትራፎርድ ተዛወረ።
የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ሮናልዶ ክለባችንን ውጤታማ ያደርግልናል የሚል ተስፋ ሰንቀው የነበረ ቢኾንም ከወቅቱ የቡድኑ አሠልጣኝ ከነበረው ኤሪክ ቴንሀግ ጋር ባለመግባባታቸው ከቀያይ ሰይጣኖች ጋር የነበረው እህል ውኃ አክትሟል።
የሳዑዲ አረቢያው ክለብ አልናስር በ2023 ለፖርቹጋላዊው ተጫዋች 200 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ደመወዝ በመክፈል ተጫዋቹ አደረገው።
በሊጉ በመጫወትም የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ እንዲነቃቃ አድርጎታል።
በርካታ ክዋክብት ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት የሊጉ ድምቀት እንዲኾኑ የተጫዎተው ሚና ከፍ ያለ ነው።
ለብሔራዊ ቡድኑ እና በተጫወተባቸው ክለቦች ውጤታማ የኾነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዕድሜው አመሻሽ ላይ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎ ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የ2026 የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ተሳትፎየ ይኾናል ብሏል።
ለተጫወተባቸው ክለቦች እና ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን 953 ግቦችን ያስቆጠረው የ40 ዓመቱ ተጫዋች በቀጣይ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ውስጥ እራሱን ከእግር ኳስ እንደሚያገል ተናግሯል።
በካናዳ፣ በሜክሲኮ እና አሜሪካ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ሮናልዶ ለስድስተኛ ጊዜ በትልቅ መድረክ ሀገሩን በመወከል የሚሰለፍ ይኾናል።
የ2026 የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው እንደሚኾን ሲ ኤን ኤን ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ሮናልዶ “በትክክል የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ጨዋታየ ይኾናል ነው” ያለው።
“ያኔ 41 ዓመቴ ይኾናል እናም ለእኔ ትልቁ የጨዋታ መድረክ ይኾናል ብዬ አስባለሁ” ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ በሳዑዲ አረቢያ ለአል ናስር ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ሮናልዶ 143 ግቦችን ለሀገሩ በማስቆጠር የምንግዜም የብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመኾን በታሪክ ስሙን ጽፏል።
ሮናልዶ ከሲ ኤን ኤኗ ቤኪ አንደርሰን ጋር ባደረገው ቆይታ “ዕውነት እንነጋገር ከተባለ በቅርቡ ማለቴ ምናልባት አንድ ወይም ሁለት ዓመት ሊኾን ይችላል እግር ኳስ በመጫወት የምቆየው” ብሏል።
ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን የ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ያሳካው እና የ5 ጊዜው የባላናዶር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ሕይወቱ 1ሺህ ግቦችን ማስቆጠር እንደሚፈልግ መናገሩ ይታወሳል።
ከ500 ሚሊዮን በላይ የኢንስታግራም ተከታዮች ያሉት ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ሕይወቱ ከዓለም ዋንጫ ውጭ ሁሉንም ዋንጫዋች አሳክቷል።
ሮናልዶ የብዙዎች የጠንክሮ መሥራት እና ለችግር እጅ አለመስጠት አርአያ ነው።
ምክኒያቱም ያኔ የሚበላው አጦ ምግብ የለመነው ሮናልዶ ዛሬ ቢሊየነር ነው። ያኔ የአባቱን የተቀደደ ጫማ ለብሶ ኳስ የመታው ሮናልዶ ዛሬ የግል ጀትን ጨምሮ ያሉትን የቅንጡ መኪኖች ቁጥር ከመብዛታቸው የተነሳ በውል አያውቃቸውና።
ዘጋቢ፦ ሀብታሙ ዳኛቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here