ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 11ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬም ሲቀጥል አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂው የሲቲ እና የሊቨርፑል ጨዋታ በኢትሀድ ስታዲየም ይደረጋል።
ምንአልባትም የደረጃ ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው ይህ ጨዋታ ሲቲ አሁን በሊጉ ያለውን ደረጃ ለማስጠበቅ እና ሊቨርፑል ተስፈንጥሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ለመምጣት ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ ይኾናል።
ሲቲ በሊግ ካፕ ስዋንሴ ሲቲን በማሸነፍ የቀደመ አቋሙን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ቡድኑ ወደ ማሸነፍ መንፈሱ ሙሉ ለሙሉ መመለሱን ያረጋገጠበትን ድል ያገኘው ደግሞ በቻምፒዎንስ ሊጉ ቦርን ማውዝን 4ለ1 ያሸነፈበት ጨዋታ ነበር።
በሊቨርፑል በኩል ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ በብሬንት ፎርድ እና በሊግ ካፕ በክርስቲያል ፓላስ በመሸነፉ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቶ የቆየው ሊቨርፑል ከወደቀበት በማንሠራራት በፕሪሚየር ሊጉ አስቶንቪላን እና በቻምፒዮንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ተመልሷል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ባደረጓቸው ሁሉም ጨዋታዎች 184 ጊዜ የተገናኙ ሲኾን 85 ጊዜ ሊቨርፑል በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲኾን ሲቲም 49 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል። ቀሪው ጨዋታ ደግሞ አቻ የተለያዩበት ነው።
ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ በተገናኙባቸው የባለፈው የፕሪሚየር ሊግ ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሊቨርፑል በማሸነፍ ቀዳሚ ሲኾን አንዱ ጨዋታ ደግሞ አቻ የተለያዩበት ነው።
ሲቲ አሁን በሊጉ ያለውን ነጥብ ከ19 ወደ 22 በማሳደግ በ26 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘውን አርሰናልን ለመጠጋት እና ቦታውን ለማስጠበቅ ሲፋለም ሊቨርፑል ደግሞ አሁን በ18 ነጥብ ካለበት ስድስተኛ ደረጃ ተስፈንጥሮ ለመውጣት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይለዋል።
ጨዋታውም ምሽት 1፡30 መካሄድ ይጀምራል።
በሊጉ ሌሎች ጨዋታዎችም ሲካሄዱ አስቶንቪላ ከቦርንማውዝ፣ ብሬንት ፎርድ ከኒውካስትል፣ ክርስቲያል ፓላስ ከብራይተን እና ኖቲንግሀም ፎረስት ከሊድስ ጋር በተመሳሳይ ሰዓት 11፡00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



