ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማንቸስተር ዩናይትድ አፍቃሪያን ጥቁሩ ወርቅ ይሉታል። ይህችን ዓለም የተቀላቀለው እንደፈረንጆቹ ዘመን ሐምሌ 11/2002 በአፍሪካዊቷ አይቮሪ ኮስት አቢጃን ከተማ ነው። የአንድ ወቅቱ ስደተኛ የአሁኑ የኦልድትራፎርድ ኮከብ አማድ ዲያሎ።
በልጅነቱ ከቤተሰቡ ጋር በስደት ወደ ጣሊያን ያቀናው አማድ ኳስን ማንከባለል የጀመረው በስደት ሀገሩ ጣሊያን ነው። የመጀመሪያ በታዳጊ ደረጃ የተጫወተበት ክለብ ደግሞ ቦካ ባርኮ የተሰኘ ክለብ ነው።
በ2015 ወደ አታላንታ አቅንቶ በአታላንታ ወጣት ቡድን ውስጥ መጫወት ጀመረ።
የተጫዋቹ የእግር ኳስ እድገት ቀጥሎ በ2019 ለአታላንታ ዋናው ቡድን መጫወት ጀመረ። በዋናው ቡድን ባሳየው ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ምክኒያትም የትልልቅ ክለቦችን ትኩረት ሳበ።
የእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ በጥር 2021 የዝውውር ወቅት ኮቲዲቯራዊኑ የመስመር ተጫዋች የግሉ አደረገ። ነገር ግን ማንቼስተር ዩናይትድ በወቅቱ ብዙ አማራጭ ተጫዋቾች ስለነበሩት በውሰት ለስኮትላንዳዊው ክለብ ሬንጀርስ ሰጥቶታል።
ተጫዋቹ በ2022/2023 የውድድር ዓመት ደግሞ ወደ ቻምፒዮንሺፕ ክለብ ሰንደርላንድ በውሰት ተልኮ በጥሩ ብቃት መጫዎት እና ታዓምራዊ እግሮቹን ማሳየት ችሏል።
በዚያው ዘመን ባሳየው ብቃትም የዓመቱ የደጋፊዎች ምርጥ ተጫዋች የሚል ሽልማት ማግኘት የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነው።
አይቬሪኮስት ያፈራችው ጥቁሩ የእግር ኳስ ፈርጥ አማድ ዲያሎ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ክለቡ ማንቼስተር ዩናይትድ ተመልሶ እየተጫወተ ይገኛል።
አማድ አሁን በኦልድትራፎርድ ጥሩ ብቃት ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
በተለይ የሚያስቆጥራቸው ግቦች በተደጋጋሚ ዩናይትድን አሸናፊ ያደረጉ ወይም ከሽንፈት የታደጊ ናቸውና በዩናይትድ ደጋፊዎች ትልቅ ቦታ እንዲያገኝ አድርጎታል።
በቅርቡ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዩናይትድ በፎረስት 2ለ1 ሊሸነፍ ጫፍ ደርሶ በአማድ ድንቅ ግብ መትረፉ ይታወሳል።
ለአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ቡድንም ወሳኝ ተጫዋቹ አማድ ፍጥነቱ፣ ኳስ ይዞ የተጋጣሚ ተጫዋቾችን በመታለል ወደ ግብ የሚቀርብበት ችሎታው እና በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት ብቃቱ ተወዳጅ እና ተመራጭ እንዲኾን አድርጎታል።
ከምንም በላይ ግን እስካሁን ካደረገው ይልቅ የሚያደግ ክህሎቱ ነገ በኦልድትራፎርድ ምን ይሠራል የሚለው የዩናይትድ አፍቃሪያን ጉጉት ነው።
በምስጋናው ብርሃኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን



