አርሰናልን ወደ ጠንካራ ተፎካካሪነት የመለሱት ሚኬል አርቴታ

0
26

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ውስጥ ተወዳጅ እና ታሪካዊ ከሚባሉ ክለቦች ውስጥ አንዱ አርሰናል ነው። አርሰናል በዓለም ላይ በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች መካከልም አንደኛው ነው።

አርሰናል አሁን ላይ በምርጥ ብቃት ላይ ይገኛል። ለዚህ ብቃቱ ደግሞ የአሠልጣኙ ድርሻ ታላቅ ነው። አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ አርሰናልን ከውጤት ቀውስ አውጥተው ወደ አስፈሪ ተፊካካሪነት መልሰውታል።

የ2025/2026 የውድድር ዘመን ጅማሮ ደግሞ የቡድኑን ጠንካራነት እያሳየ ነው። በአርሰናል ቤት የተጫወቱት እና አርሰናልን እያሰለጠኑ ውጤታማ ያደረጉት ሚኬል አርቴታ እ. አ.አ መጋቢት 26/1982 ነበር በስፔን ሳን ሴባስቲያን የተወለዱት።

እኒህ ሰው በእግር ኳሱ ታዋቂ በኾነ አካባቢ ላይ መወለዳቸው አሁን ላሉበት ቦታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይነገራል።

ያደጉበት አካባቢ ለእግር ኳስ የነበራቸውን ፍቅር እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሚኬል አርቴታ የእግር ኳስ ሕይዎታቸው የሚጀምረው አንቲጓኮ በሚባል የአካባቢው የወጣት ክለብ ውስጥ ነው።

በዚህ ክለብ ውስጥ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እና ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋች ከኾነው ዣቢ አሎንሶ ጋር የቅርብ ጓደኞች እንደነበሩም ይነገራል። ሁለቱ ጓደኛሞች ብዙውን ጊዜ ሳን ሴባስቲያን የባሕር ዳርቻዎች ላይ አብረው እግር ኳስ ያንከባልሉም ነበር። ሞኬል አርቴታ የባሕር ዳርቻ እና እግርኳስን እንደሚወዱ ቢቢሲ አርቴታን ሕይወት በዳሰሰበት ዘገባው መዝግቧል።

ገና ታዳጊ እያሉ የእግር ኳስ ተሰጧቸው በታዋቂው የባርሴሎና የወጣቶች አካዳሚ ላ ማስያ ታይቶ ተደነቀ። ወደ ከዋክብቱ መፍለቂያ አካዳሚም ገቡ። በላ ማስያ ከእግር ኳስ ከዋክብት ጋር ተገናኙ።

ይህ በባስክ በጀመረው እና በባርሴሎና የወጣት አካዳሚ የተቀረጸው የልጅነት ዕውቀታቸው አሁን ላይ በአርሰናል ውጤታማ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል። በጠንካራ አካዳሚ ማደጋቸው የእግር ኳስ ዕውቀት እና ጠንካራ የሥራ ሥነ ምግባር እንዲያዳብሩ አግዟቸዋል።

የወጣትነት ጊዜያቸውን ባርሴሎና ውስጥ ያሳለፉት አርቴታ ለፓሪስ ሴንት ዠርሜን፣ ሬንጀርስ እና ሪያል ሶሲዳድ ተጫውተዋል።

በእንግሊዝ እግር ኳስ ውስጥ በኤቨርተን እና በአርሰናል የተጫወቱት አርቴታ በአርሰናል የክለቡ አምበልም ነበሩ። በአርሰናል ቆይታቸው ሁለት የኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችንም አሸንፈዋል።

እ.አ.አ በ2016 ራሳቸውን ከእግር ኳስ ተጨዋችነት ካገለሉ በኋላ የአሠልጣኝነት ሥልጠናዎችን ወስደዋል።
ከዚያም በኋላ የሀገራቸው ልጅ የፔፕ ጋርዲዮ ምክትል አሠልጣኝ ኾነው በማንቸስተር ሲቲ ቤት ሠርተዋል።

ማንቸስተር ሲቲ በፔፕ ጋርዲዮላ ሥር ውጤታማ ሲኾን የሚኬል አርቴታ አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነበር። በማንቸስተር ሲቲ ቤት ባሳዩት የአሠልጣኝነት ተስፋ በቀድሞ ክለባቸው እይታ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው።

በወቅቱ በውጤት ቀውስ ውስጥ የነበረው አርሰናል የቀድሞ ልጁን አስፈረመ። ሚኬል 2019 የአርሰናል ዋና አሠልጣኝ በመኾንም ተሾሙ።

አርቴታ በአርሰናል ኀላፊነትን ከወሰዱ በኋላ በ2019/2020 የውድድር ዓመት የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን እና የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫን አሸንፈዋል። ቀስ በቀስ ቡድኑ ርቆበት ወደ ነበረው የአሕጉር ውድድር መለሱት። አሁን ላይ በአውሮፓ ምርጥ ከሚባሉ እና በቀላሉ ከማይሸነፉ ቡድኖች መካከል አድርገውታል።

ሚኬል አርቴታ አርሰናልን በማደስ እና ወጣት ተጨዋቾችን በማሳደግ ይታወቃሉ።

አርሰናልን ባለፉት ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ሁነኛ ተፎካካሪ ያደረጉት ሚኬል አርቴታ በ2025/26 የውድድር ዘመን የዋንጫ አሸናፊ እንደሚኾኑ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ፕሪምዬር ሊጉን እየመሩ የሚገኙት አርሰናሎች በሚኬል አርቴታ ሥር ጠንካራ መኾናቸውን አስመስክረዋል። አሠልጣኙ በጥቅምት ወር ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ድል አድርገዋል። ይህ ደግሞ ጥንካሬያቸውን በሚገባ የሚያሳይ ነው። አርሰናል አሁን ላይ በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት ክለብ አይደለም። በሁሉም ውድድሮች ወጥ አቋም በማሳየት በአስደናቂ ጉዞ ላይ ነው።

በሁሉም ውድድሮች ውጤታማ ጉዞ ላይ ያሉት አርቴታ ዘንድሮ በዋንጫ የሚሞሸሩበት ዓመት እንደሚኾን ይጠበቃል።

በምስጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here