ተጠባቂ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

0
27

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ዙር ጨዋታ ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል በርንለይ አርሰናልን የሚያስተናግድበት፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ኖቲንግሀም ፎረስት ተጉዞ ጨዋታውን የሚያደርግበት እና ሊበርፑል በሜዳው አስቶቪላን ጋብዞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ጨዋታዎች ናቸው።

በተከታታይ በሊጉ እያሸነፈ ጥንካሬውን እያሳየ የሚገኘው አርሰናል ዛሬ ወደ በርንለይ ተጉዞ ቀን 12፡00 ሰዓት ላይ የሚያደርገውን ጨዋታ የስፖርት አፍቃሪው የሚጠብቀው ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙበት 18 ያህል የሊጉ ጨዋታ አርሰናል የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

አርሰናሎች ከወቅታዊ አቋም ጋር ሲታዩ ባለፉት በሊጉ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አለመሸነፋቸው እና በሦስቱ ደግሞ መረባቸው አለመደፈሩ የቡድኑን ጠንካራ የመከላከል ብቃት ያሳያል።

የዛሬው ጨዋታ አንድ ሌላ የታሪክ አጋጣሚም ይዞ ብቅ ብሏል አሠልጣኙ ሚኬል አርቴታ በክለቡ ተጨዋች በነበረበት ጊዜ አርሰናል በተከታታይ አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርበት ሲያሸንፍ በሁሉም ጨዋታዎች ተሰልፎ መጫዎቱ እና ይህን ሪክርድም በአሠልጣኝነት ዘመኑ ለመጋራት መቃረቡ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

አርሰናሎች እስካሁን ባሳዩት አቋም ግቦችን የሚያስቆጥሩት አብዛኛው ከቆመ ኳስ መኾኑ እና በሊጉ ካስቆጠሯቸው 16 ግቦች 11 ያህሉ የቆሙ ኳሶች ናቸው።

የአርሰናል ተጋጣሚ በርንሌይም በአርሰናል ላይ ካደረጋቸው 18 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ አለማስቆጠሩ ደካማ ቡድን ለመኾኑ ማሳያ ነው። ቡድኑ እስካሁን በሊጉ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች ዘጠኝ ብቻ መኾናቸው የበርንለይን ደካማ አቋም የሚያሳይ ነው።

ቡድኑ ከቅርብ ጊዜ ብቃት አኳያ ሲታይ በሊጉ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፉ እና ለሦስተኛ ድል የሚጫወት መኾኑ ለአርሰናሎች በቀላሉ ላይሸነፍ የሚችልበት ዕድልም አለ።

ሌላው የዛሬ የሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ኖቲንግሀም ፎረስት ተጉዞ ቀን 12፡00 ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ነው።

ዩናይትዶች ሲወቀሱበት ከነበረው የሽንፈት ድባቴ ወጥተው ወደ አሸናፊነት መመለሳቸው ሊጉ ተፎካካሪ ከመኾን በተጨማሪ ለሊጉ ፉክክር ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገም ይገኛል።

ዩናይትዶች በተከታታይ ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማሸነፋቸው ለክለቡ ደጋፊዎች ትልቅ ብስራት ሲኾን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ ደግሞ ወደ ቀደመ ብቃታቸው ለመመለሳቸው ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ በመኾኑ ጨዋታውን እጅግ ተጠባቂ ነው የሚያደርገው።

ክለቡ በጥቅምት ወር መቶ በመቶ አሸናፊ ከኾኑ ሦስት ክለቦችም አንዱ ለመኾንም በቅቷል።

ዩናይትድ ከሦስተኛው ዙር ጨዋታ ጀምሮ ከአርሰናል በመቀጠል ከፍተኛውን ነጥብ የሠበሠበ ክለብ ሲኾን በሊጉ 14 ግቦችንም ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። የቡድኑ ሞተር እየኾነ የመጣው ብራያን ምቦሞ ከኤርሊንግ ሃላንድ እና ሞሃመድ ሳላህ ቀጥሎ በጣም ብዙ ግብ የኾኑ ኳሶችን በማመቻቸት ስሙ በክለቡ ከፍ እያለም መጥቷል።

ማቲዎስ ኩኛም ሦስት ግቦችን እና አራት ያለቀላቸው ኳሶችን በማቀበል ለክለቡ ሌላው ባለውለታ ነው።

ለዩናይትድ የማይመለሰው ፎረስት ባለፉት ጊዜያት በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ማንቼስተር ዩናይትድን ማሸነፍ መቻሉ ዛሬም ለዩናይትድ የማይመለስ ክለብ እንደኾነ አመላካች ነው።

ቡድኑ አራት ተከታታይ ድልን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘው ከ1909 እስከ 1910 ባለው የጨዋታ ዘመን ነው። ፎረስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕሪሚየር ሊጉ ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ስድስቱን መሸነፉ እና የግብ ማጣት ችግሩ የክለቡ ሌላው ችግር ነው።

በተከታታይ አራት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ጎል ሳያስቆጥር መሸነፉ የቡድኑን ደካማነት ያሳያል። ክለቡ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የመሸነፍ ሪከርድ ያስመዘገበው በ2004 ነበር።

ሌላው የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ ሊበርፑል በሜዳው አስቶቪላን የሚጋብዝበት ጨዋታ ነው። ሊቨርፑል በተደጋጋሚ በመሸነፍ ያለፈው ዓመት ጥንካሬው የት ገባ አስብሎታል። በሜዳው ጭምር አሳፋሪ ሽንፈት እየገጠመው ያለው ቡድኑ በአንፊልድ ጥሩ ታሪክ ያለው ክለብ ነው።

በሜዳው የዛሬውን ተጋጣሚውን አስቶንቪላን ከሰባት ጨዋታዎች ስድስቱን ማሸነፍ የቻለ ክለብም ነው። ጥያቄው የሊቨርፑል የቀድሞ ጥንካሬው በመጥፋቱ ዛሬ ይመለሳል ወይስ የቁልቁለት ጉዞውን ይቀጥላል የሚለው ምሽት 5፡00 ላይ የሚታይ ነው የሚኾነው።

ሊቨርፑል በተከታታይ አራት ጨዋታ መሸነፉ አስደንጋጭ አድርጎታል። ክለቡ ዛሬ የሚሸነፍ ከኾነ ከ1953 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ታሪክን የሚጽፍ ይኾናል።

ሊቨርፑል በአንድ የውድድር ዓመት የመጀመሪያዎቹን አምስት ጨዋታዎች አሸንፎ ቀጣዮቹን አራት በተከታታይ የተሸነፈ በእንግሊዝ ከፍተኛ ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው ክለብም ኾኗል። በረጅም ኳሶች እየተጠቃ ያለው ክለቡ ዛሬ አሠልጣኙ ይህን ችግር ፈትተው ወደ አሸናፊነት ሊመልሱ ይችላሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ተጋጣሚው አስቶን ቪላ በአሁኑ ጊዜ አራት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ቡድን መኾኑ ዛሬ ለሊቨርፑል ላይመለስ የሚችልበት ሁኔታም አለ። ሁለቱ ክለቦች አንዱ ወደ አሸናፊነት ሌላው ደግሞ ያለውን የአሸናፊነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው የሚጥሩት።

ሌሎች የሊጉ ጨዋታዎችም ዛሬ ሲደረጉ ቸልሲ ከ ቶተንሃም፣ ብራይተን ከሊድስ፣ ክርስታል ፓላስ ከብሬንት ፎርድ እና ፉልሀም ከወልቨስ በተመሳሳይ ሰዓት ቀን 12፡ 00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በምስጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here