አዲስ አበባ: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ጸሐፊ ባሕሩ ጥላሁን በ2017 ዓ.ም በእግርኳስ ልማት፣ በሥልጠና እና ውድድር በርካታ ሥራዎች መከናዎናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በከፍተኛ የበጀት ጫና ውስጥ ኾኖም በሁሉም የዕድሜ እርከኖች አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጨዋታዎችን ማድረጉን አብራርተዋል።
በተለይ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚጫወትበት ኹኔታ ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑን ለከፍተኛ የበጀት እጥረት መዳረጉን አንስተዋል። በበጀት እጥረት ምክንያትም በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የወንዶች ውድድር ተሳትፎ ሳይደረግ መቅረቱን ነው ያስረዱት።
ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው አለመጫዎቱ ከሜዳ እና ደጋፊዎች ያገኝ የነበረውን ዕድል እና ውጤት አጥቷል ነው ያሉት።
መንግሥት በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ያነሱት አቶ ባህሩ አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ብሔራዊ ቡድኑ የካፍ ስታንዳርድን የሚያሟላ ስታዲየም አለመኖሩን ተከትሎ አሁንም ከሀገር ወጥቶ እየተጫወተ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የሚያስችሏትን መሠረተ ልማቶች እያሟላች መኾኑንም አንስተዋል። በንቅናቄ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ያሰኑት ፕሬዝዳንቱ ይህም የተጀመሩ ስታዲየሞችን የማጠናቀቅ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎችን በሀገሩ እንዲያደርግ ይረዳዋል ነው ያሉት።
ዓመቱ ክለቦች ፌዴሬሽኑ በጉባኤ ያጸደቃቸውን ሕጎች ወደጎን በመተው ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እና ስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት (ካስ) የወሰዱበት እንደነበር አንስተዋል።
ፌዴሬሽኑ በጉባኤ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች በባለቤትነት የሚወስዱ ክለቦችም ሕጎችን ማክበር እንዳለባቸው የተማሩበት ዓመት መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለ ኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



