ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በዓለም ዋጫ ማጣሪያ ምክንያት ተቋርጦ ነው የቆየው። ክለቦችም በዚሁ ጨዋታ ምክንያት እረፍት ላይ ይገኛሉ። ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመለሱት የፊታችን ቅዳሜ ይኾናል።
ከእረፍት የሚመለሰው ማንቸስተር ዩናይትድም በአሠልጣኝ ሩበን አሞሪም እየተመራ ወደፊት በሊጉ ያለውን እጣ ፈንታ የሚያሳይበትን ጨዋታ ነው የሚያደርገው። ቡድኑ ያለውን ዕድል የሚወስንበትን አራት ወሳኝ ጨዋታዎችን ያደርጋል።
ዩናይትድ ከእረፍቱ በፊት ሰንደርላንድን 2ለ0 በማሸነፍ በብሬንትፎርድ ባጋጠመው ከባድ ሽንፈት ሳቢያ በአሞሪም ላይ ተጭኖ የነበረውን ግፊት ማቅለል ችሎም ነበር።
ይህ ድል የአሞሪምን ቡድን ወደ 10ኛ ደረጃ ቢያሳድገውም አሠልጣኙ ወደ ክለቡ ከተቀላቀለ ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር በኋላ ካደረጋቸው 34 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 10 ጨዋታዎች ላይ ብቻ መኾኑ አሁንም አሠልጣኙ ከጫና እንዳልተላቀቀ አመላካች ነው።
የክለቡ አክሲዮን ተጋሪ ሰር ጂም ራትክሊፍ ለአሞሪም ድጋፍ ቢሰጡም ቡድኑ ባለፈው የውድድር ዓመት ካገኘው 15ኛ ደረጃ በቸሻለ ከፍ የማድረግ ኀላፊነት ግን አሁንም አለበት።
ዩናይትድ እስካሁን ተከታታይ ሁለት የሊግ ድሎችን ማስመዝገብ አለመቻሉም ለአሠልጣኙ ሌላ የራስ ምታት ነው።
ዩናይትድ የፊታችን እሑድ አንፊልድ ላይ ከጠንካራዎቹ ሊቨርፑል ጋር በሚደረገው ጨዋታ ፈተናውን ሲጀምር ብራይተንን በሜዳው፣ ኖቲንግሃም ፎረስትን እና ቶተንሃምን ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ በማግኘት የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሊጉ ወደ ፊት ለመስፈንጠር ወሳኝ ኾነው ተገኝተዋል።
እነዚህ ጨዋታዎች ክለቡን በሊጉ ወደ ፊት ለመግፋት ትልቅ ዕድል ቢኾኑም ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በተመሳሳይ ሽንፈት እንደገጠመው ታሪኩ ያሳያል።
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!