ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት፦

0
12
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ነው። የ2026 የዓለም የወንዶች እግር ኳስ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት ደግሞ ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ ናቸው።
ለዚህ ውድድር ሀገራት ትኬታቸውን ለመያዝ የሚያደርጉት ትግል አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል። ከሰሞኑም የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና የእስያ ሀገራት ጨዋታቸውን አድርገዋል።
48 ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር እስካኹን 28 ሀገራት ትኬታቸውን ቆርጠዋል።
አስተናጋጆቹ ሀገራት ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ስቴትስ በቀጥታ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።
እንግሊዝ ከአውሮፓ ቀድማ ለዓለም ዋንጫው ትኬቷን መያዝ የቻለች ሀገር መኾን ችላለች።
ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለፈችውን ኬፕ ቨርዴ ጨምሮ አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱኒዚያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።
ከእስያ ሀገራት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለፉትን ጆርዳን እና ኡዝቤኪስታንን ጨምሮ አውስትራሊያ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ ማለፋቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።
ጠንካራ ፉክክር የታየበት የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ፉክክር ደግሞ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ፓራጓይ እና ኡራጓይ ከወዲሁ ማለፋቸውን ያረጋገጡበት ማጣሪያ ኾኗል።
ከኦሽንያ ኒውዚላንድ በብቸኝነት እስካሁን ማለፏን ያረጋገጠች ሀገር መኾንም ችላለች።
ኬፕ ቨርዴ፣ ጆርዳን እና ኡዝቤኪስታን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ናቸው።
በመጭዎቹ ጊዜያት ተጨማሪ ሀገራት የማጣሪያ ውድድሮችን በማጠናቀቅ ትኬታቸውን ያገኛሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here