ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ2025/2026 የውድድር ዘመን እየተሳተፈ የሚገኘው ኒውካስትል ዩናይትድ እስካሁን ሰባት ጨዋታዎችን አድርጎ ማሸነፍ የቻለው ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው።
በሁለቱ ተሸንፎ በሦሥት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
ማግኘት ከነበረበት 21 ነጥብ የያዘው ዘጠኝ ነጥብ እና አንድ ንጹህ የግብ ክፍያ ነው።11ኛ ደረጃ ላይም ይገኛል።
ውጤቱ ያላስደሰተው የክለቡ ቦርድ አዲስ የስፖርት ዳይሬክተር ለመሾም ኹነኛ ባለሙያ ሲያፈላልግ መሰንበቱን ስካይ ስፖርት አስታውሷል።
ክለቡ ዛሬ ባወጣው መግለጫም ፖል ሚቼልን አንስቶ የኖቲንግሃም ፎረስት ዋና የእግር ኳስ ኀላፊ የነበሩትን ሮስ ዊልሰንን የስፖርት ዳይሬክተር አድርጎ መሾሙን አስታውቋል።
ዊልሰን ቀደም ሲል በሬንጀርስ የስፖርት ዳይሬክተር እና በሳውዝሃምፕተን የእግር ኳስ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር እንደነበሩ ስካይ ስፖርት ጨምሮ አስነብቧል።
ተሿሚው የስፖርት ዳይሬክተር የኒውካስትልን ውጤት ሊያሻሽል የሚችል ዕቅድ ይዘው እንደሚቀርቡም ተናግረዋል ነው የተባለው።
የኒውካስትል ዩናይትድ ዋና አሠልጣኝ ኤዲ ሃው በበኩላቸው ከዊልሰን ጋር አብሮ የመሥራት እድልን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ክለቡም በዳይሬክተሩ አማካኝነት ግልጽ ስትራቴጂ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!