ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ብሬንትፎርድ በሜዳው ማንቸስተር ዩናይትድን ቀን 8:30 ተኩል ያስተናግዳል። ብሬንትፎርድ ከአምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፏል። በአንዱ አሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈም ከሚገኝበት 17ኛ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማለት ያስችለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ በአንጻሩ እስካሁን ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ፣ በሁለቱ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ ሰባት ነጥብ በመያዝ 11ኛ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ለየራሳቸው ከፍተኛ የኾነ የደረጃ ለውጥ የሚያመጣ በመኾኑ ተጠባቂ አድርጎታል። በሌላ ጨዋታ እስካሁን ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ15 ነጥብ የሊጉ መሪ የኾነው ሊቨርፑል ቀን 11:00 ላይ ከሜዳው ውጭ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ክሪስታል ፓላስን የሚገጥምበት ጨዋታ ወሳኝነት አለው። ሊቨርፑል አንደኛነቱን ለማስጠበቅ ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።
በተመሳሳይ ቀን 11:00 ላይ በሰባት ነጥብ ዘጠነኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው በአራት ነጥብ 16ኛ ላይ ከሚገኘው በርንሌይ ጋር ይገናኛል። የዚህ ጨዋታ አሸናፊ ቡድን ደረጃውን ያሻሽላል ማለት ነው። ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቼልሲ በሜዳው 14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ብራይተን ጋር ይጫወታል። በተመሳሳይ ቀን 11:00 በፕሪሚየር ሊጉ በሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊድስ ዩናይትድ በ10 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦርንማውዝ ጋር ይጫወታል።
ምሽት 1፡30 ከአምስት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ በመያዝ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኖቲንግሃም ፎረስት ሰባተኛ ላይ የሚገኘውን ሰንደርላንድን ይገጥማል። በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ አሸንፎ ፣ በአንድ ተሸንፎ እና አቻ ተለያይቶ 10 ነጥብ በመያዝ በአርሰናል በአንድ ንጹህ የግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ የኾነው ቶተንሃም ያለምንም ነጥብ መጨረሻ ላይ ከሚገኘው ወልቨርሃምፕተን ጋር ምሽት 4:00 ላይ ይጫወታል።
ቶተንሃም ጨዋታውን ካሸነፈ የሁለተኛ ደረጃን ከአርሰናል የሚረከብ ይኾናል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል። ሊጉን ሊቨርፑል ይመረዋል፤ አስቶን ቪላ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ እና ወልቨርሃምፕተን ወንደረርስ ወረጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ ሲል ቢቢሲ በድረ ገጹ ተንትኗል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



