ባሕር ዳር፡ መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት አበባው ድረስ ይባላል፤ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው። ቀደም ሲል የአስፓልት መንገድ ላይ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበር አስታውሶናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በእረፍት ቀኑ ወደ ሚሊኒየም ስፓርት ማዘውተሪያ እና ሌሎች ሜዳዎች በማቅናት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ገልጾልናል። የሚሊኒየም ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ስፖርትን ጨምሮ ትልልቅ ሁነቶች ይካሄዱበታል ብሎናል።
ወጣቱ ካለው የስፖርት ፍቅር አንጻር ችግሩን ችሎ ይጠቀማል እንጅ በዙሪያው ከስፖርቱ ጋር የማይሄዱ እና የከተማ ገጽታ የሚያበላሹ ነገሮችን እንደሚመለከት ነው የገለጸልን። እንደ ከተማ አሥተዳደርም ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም ብሎናል።
የሜዳው ምቹ አለመኾን፤ የውኃ መያዣ ፕላስቲክ መከማቻ መኾን፤ ተገቢ አጥር ባመኖሩ ከደኅንነት አንጻር አስጊ መኾን፣ የአንዳንድ ሰዎች በዙሪያው መጸዳዳት፣ ያለውን መጸዳጃ ቤት በአግባቡ አለመጠቀም እና ሌሎች አላስፈላጊ ተግባራትን በዙሪያው የመከወን ሁኔታ እንዳለ ነው የገለጸው።
ባሕር ዳር ትልቅ ከተማ ናት፤ ነገር ግን በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ የለም ነው ያለን። በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ያስፈልጋል፤ አዳዲስ ሰፈሮች ሲለሙ እና መሠረተ ልማቶች ሢሠሩ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ታሳቢ መደረግ አለባቸው ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና ተቋማት ኮንትራት አሥተዳደር ባለሙያ መልሰው ወርቁ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ቁጥራቸው አስር የሚደረሱ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች መኖራቸውን ነግረውናል።
ከእነዚህ መካከል ሕጋዊ ካርታ ያላቸው አምስት ናቸው ብለዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ ካርታ የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። በሁሉም ክፍለ ከተማ ሜዳዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ባለሙያው ካርታ የሌላቸው ካርታ እንዲኖራቸው እየሠሩ እንደኾነ ጠቅሰዋል። በዓመት አንድ ሜዳ በጀት ተይዞ እና ካርታ ተዘጋጅቶ ቢሠራ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ ችግር ይቀረፋል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቶማስ ታምሩ ባሕር ዳር የስፖርት ቱሪዝም ከተማ ናት ብለዋል። ከተማዋ ካላት የመልማት ፍላጎት፤ ካላት ስፖርት ወዳድ ማኅበረሰብ እና የስፖርት ሜዳዎች ተጠቃሚ ቁጥር አንጻር የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ በቂ አይደለም፤ እንደ ከተማ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ምቹ ለማድረግ እና ለማስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች አንዳንዶች ብዙ ወጣቶች የሚያዘወትርባቸው እና ምቹ እንደኾኑ ነግረውናል። ምቹ ያልሆኑ እና ብዙ ሥራ የሚጠይቁ አሉ ነው ያሉት።
ለስፖርት ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው፤ ረጅም ዓመት አገልግሎት የሰጠው እና አሁንም እየሰጠ ያለው ሚሊኒየም የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ መሀል ከተማ ላይ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ብዙ የቆሻሻ እና የፕላስቲክ የውኃ መያዣዎች ሲከማቹበት እንደነበርም ገልጸዋል። ለቦታው የማይመጥኑ ከስፖርት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሕገ ወጥ ጨዋታዎች እና ተግባሮች እንደሚፈጸሙበትም ነግረውናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በምክትል ከንቲባ ደረጃ እየተመራ ከደንብ ማስከበር፣ ጽዳት እና ውበት ባለሙያዎች ጋር በመኾን የማጽዳት እና ሕገ ወጥ ተግባሮችን የሚከውኑትን የማስነሳት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከነበረው ሁኔታ አንጻርም ከፍተኛ ለውጥ እንደታየበት ጠቅሰዋል። ቀሪ ሥራዎች ግን አሉ ነው ያሉት። “ባሕር ዳር ከተማን በስፖርቱ ዘርፍ ለሌሎች የተሞክሮ መቀመሪያ ከተማ ማድረግ አለብን”በሚል አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል።
አጥራቸውን ማጠናከር፣ ሜዳዎቹን ምቹ ማድረግ፣ አስተማማኝ ጥበቃ ያለው ማድረግ እና ብዙ ወጣቶች ሜዳውን እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ማኅበረሰብ ስፖርታዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሥራዎች ሢሠሩ አጋዥ መኾኑንም አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች አንዳንዶች ሕጋዊ ካርታ ያላቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ የአረንጓዴ ደብተር ያላቸው እና ብዙዎች ጥያቄያቸው ያልተፈታ መኾናቸውን አንስተዋል። በቀጣይ ሕጋዊ የማድረግ ተግባር ይከናወናል ነው ያሉት።
የአስፖልት መንገዶችን ዘግተው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እና የሚጫዎቱ ሰዎች መኖር ግን የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እጥረት በመኖሩ እንዳልኾነ ተናግረዋል።
አንዳንድ ሜዳዎች ምቹ ባለመኾናቸው ወጣቶች ያንን መጋፈጥ አይፈልጉም ብለዋል። በዚህ ረገድ በደንብ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እና በሳይንስ ተንትኖ ማስረዳት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።
አሁን ላይም ለአብዛኛዎቹ ወጣቶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በመሥራት ከጎዳና ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ጨዋታ ወደ ስፓርታዊ ሜዳዎች የመመለስ ተግባር ተሠርቷል፤ የሚቀር ነገር ግን አለ ነው ያሉት።
ቀጣይ የባሕር ዳር ከተማን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከልነት ለማጉላት በሚሠሩ ተግባራት የስፖርት ቤተሰቡ እና አጋር አካላት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!