አሰልችው የኢሳክ ዝውውር ዛሬ መቋጫውን የሚያገኝ ይመስላል።

0
130
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር ዛሬ ምሽት ይጠናቀቃል። ለወራት በቆየው በዚህ የዝውውር ጊዜ ታላላቆቹ የእንግሊዝ ክለቦች የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል።
የዝውውሩ የመጨረሻ ቀን ላይም በርካታ ዝውውሮች እንደሚከናውኑ ይጠበቃል። ከእነዚህ የመጨረሻ ቀን ተጠባቂ ዝውውሮች መካከል የኒውካስትሉ አሌክሳንደር ኢሳክ መጨረሻ የብዙዎች ትኩረት ነው። ሊቨርፑል ኢሳክን ለማስፈረም ወራትን የተሻገረ ጥረት አድርጓል። ስዊድናዊው አጥቂም የቀዮቹን መለያ ለመልበስ በጉጉት የዝውውሩን መጠናቀቅ ሲጠብቅ ሰንብቷል። ነገር ግን ኒውካስትል ተጨዋቹን ለመልቀቅ ባለመፈለጉ ዝውውሩ አሰልቺ ኾኖ ዛሬ ላይ ደርሷል። ሊቨርፑል ኢሳክን ለማስፈረም 115 ሚሊዮን ፖውንድ አቅርቦ በኒውካስትል ውድቅ ተደርጎበታል። ይህን ተከትሎ ኒውካስትልን ለመቀላቀል ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው ኢኪቲኬን ሊቨርፑል ጣልቃ በመግባት ከኒውካስትሎች ነጥቋል። ይህ የኢሳክን የዝውውር ሂደት በእልህ የተሞላ እንዲኾን አድርጎታል።
ኢሳክ ካለፈው ዓመት ውድድር መጠናቀቅ በኋላ የኒውካስትልን መለያ አለበሰም። ለክለቡ መጫወት እንደማይፈልግ በይፋ መግለጹን ተከትሎም በክለቡ ደጋፊዎች ይሁዳ የሚል ስም ወጥቶለታል። ፎቶውን በአደባባይ ያቃጠሉ ደጋፊዎችም ታይተዋል። ይህ የክለቡ እና የተጨዋቹ ሆድ እና ጀርባ መኾን ኢሳክን ወደ ሌላ ክለብ መሄዱን የግድ እንደሚያደርገው የተለያዩ ምንጮች ሃሳብ ነው። ቴሌግራፍ ባስነበበው ትኩስ ዜናም ኒውካስትል ከሊቨርፑል የቀረበለትን 130 ሚሊዮን ፓውንድ ለመቀበል ተስማምቷል። ተጨዋቹም ዛሬ ወደ አንፊልድ በመጓዝ የህክምና ምርመራውን ያደርጋል ብሏል ዘገባው። ይህም የክረምቱን አሰልቺ የዝውውር ወሬ መቋጫ እንደሚያበጅለት ተገምቷል።ኒውካስትል ኒክ ወልቲሜድን የክለቡ ክብረ ወሰንን በማሻሻል ማስፈረሙ ይታወሳል። ተጨማሪ አጥቂ ለማስፈረም ዛሬ ገብያ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋልም ተብሏል።
ዘጋቢ:- አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here