ደሴ: ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ “ስፖርት ለዓባይ” በሚል መሪ መልዕክት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በደሴ ከተማ መካሄድ ጀምረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ይህይስ ኃይሉ በደሴ ከተማ አሥተዳደር ስፖርት ምክር ቤት አዘጋጅነት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዚህ መድረስን አስመልክቶ “ስፖርት ለዓባይ” በሚል መሪ መልዕክት የስፖርት ፌስቲቫል ተጀምሯል ብለዋል። ዛሬ የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጎዳና ላይ ተካሂዷል ብለዋል። በመተባበር የጀመርነው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዚህ በመድረሱ ተደስተናል ነው ያሉት ተሳታፊዎች። በሳምንት ሦስት ቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንሠራለን ያሉት ተሳታፊዎቹ የዛሬውን ለየት የሚያደርገው የሕዳሴ ግድብ አፈጻጸምን አስመልክቶ የተሠማንን ደስታ ለመግለጽ በመኾኑ ነው ብለዋል። በቀጣይ ቀናት መርሐ ግብሩ የሚቀጥል ሲኾን የብስክሌት እና የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮችም እንደሚደረጉ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን