ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ዙር እጣ ድልድል ምሽቱን በሞናኮ ይፋ ኾኗል።
የውድድር ዓመቱ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ፑሽካሽ አሬና ይከናወናል። በእጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱ ላይ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የሚያዘጋጃቸውን ሁሉንም የክለብ ውድድር ዋንጫዎችን ያሸነፈው ብቸኛ ክለብ ቼልሲ የማስታወሺያ ሽልማት ተበርክቶለታል። ዝላታን ኢብራሂሞቪች ደግሞ የ2025 የዩ ኤ ፋ የፕሬዝዳንት ሽልማት አሸናፊ ኾኗል።
በብራዚላዊው ካካ እና ስዊድናዊው ታሪካዊ ተጫዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪች መሪነት በወጣው ድልድል 36 ክለቦች ተሳታፊ ይኾናሉ።
በእጣ ድልድሉ መሠረት በጉጉት የሚጠበቁ ጨዋታዎች በርክተው ታይተዋል። አርሰናል ከባየርን ሙኒክ፣ ኢንተር ሚላን እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አጓጊ ኾኗል። ቼልሲ በበኩሉ ከባርሰሎና እና ባየርን ሙኒክ ጋር የመጫወት ግዴታ ተጥሎበታል። በዚህ ዙር እያንዳንዱ ክለብ ስምንት ጨዋታዎችን ያከናውናል። ባለፈው ዓመት የተጀመረው አዲሱ ፎርማት ክለቦች በሚሰበስቡት ነጥብ መሰረት ከ1 እስከ 8 የሚጨርሱት ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያልፋሉ። ከ9 እስከ 24 የሚጨርሱ ደግሞ እርስ በእርስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርገው አሸናፊዎቹ ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላሉ። ከ25 እስከ 36 የሚጨርሱ ክለቦች ከውድድሩ ይሰናበታሉ። በዘንድሮው ውድድር እንግሊዝ ስድስት ክለቦችን በማሳተፍ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!