ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 2025/2026 የውድድር ዘመን ባለፈው ሳምንት ተጀምሯል።
የሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ደግሞ ትናንት ምሽት ቼልሲ ዌስትሃምን 5ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ ተጀምሯል። ከእነዚህ መካከል ማንቸስተር ሲቲ ከቶትንሃም ሆትስፐርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። በዚህ ጨዋታ የተሻለ ፉክክር እንደሚኖር ነው የሚጠበቀው። ሁለቱ ክለቦች በቅርብ ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ሲቲ ማሸነፍ የቻለው አራት ጊዜ ብቻ ነው። ስድስቱን ቶትንሃም ሲያሸንፍ በቀሪው ነጥብ ተጋርተዋል።
የሲቲው ሃላንድ በሊጉ 48 ጨዋታዎች 48 ግቦችን አስቆጥሯል። ይህ ተጫዋች በዛሬው ጨዋታ ከዚህ በፊት በ50 ጨዋታዎች 50 ግቦችን ማስቆጠር የቻለውን የአለን ሺረር ሪከርድ ሊጋራ ወይም ሊበልጥ ሚመችልበት ዕድል አለው።
አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በሥራ ዘመኑ እስካሁን ብዙ የተሸነፈው በሊቨርፑል ያውም 10 ጊዜ ሲኾን በሁለተኝነት በስፐርስ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። ቶትንሃም ሆትስፐርስ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በኤቲሀድ ስታዲየም ካደረጋቸው የመጨረሻ አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው ግማሹን ነው። ይህም ቡድኑ በዚህ ሜዳ ላይ የማሸነፍ ታሪኩ ጥሩ በመኾኑ ዛሬም ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል ይኖረዋል።
ዛሬ ሁለቱ ቡድኖች የሚፋለሙበት የኤቲሀድ ስታዲየም ከዚህ በተደረጉት በፊት በተደረጉ አራት የሊጉ ጨዋታዎች 21 ግቦችን አስተናግዷል። ሲቲ ዘጠኝ እና ስፐርስ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።
አሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ከዚህ ቀደም የብሬንትፎርድ አሠልጣኝ በነበሩበት ጊዜ በኤቲሀድ ስታዲየም ማንችስተር ሲቲን 2ለ1 አሸንፎ ነበር። ዛሬስ? የሚለው ደግሞ ተጠባቂ ነው። ጨዋታውም 8፡30 የሚካሄድ ይኾናል። ሌላው የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ አርሰናል በአትሌቲክስ ስታዲየም ከሊድስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ነው። ሁለቱ ቡድኖች የውድድር የመጀመሪያ ሳምንታቸውን በድል ስለጀመሩ ጥሩ የሥነ ልቦና ኹኔታ ላይ ነው የሚገኙት። አርሰናል ማንችስተር ዩናይትድን እና በተመሳሳይ ሊድስ ኤቨርተንን 1ለ0 አሸንፈዋል። አርሰናል ከሊድስ ጋር በተገናኘባቸው 14 ጨዋታዎች አልተሸነፈም 12 አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።
የአርሰናል አዲስ የፈረመው ቪክቶር ጂዮክሬስ በመጀመሪያ ጨዋታው ምንም ሙከራ ያላደረገ ሲሆን፣ የሊድስ አዲስ ፈራሚ የሆነው ሉካስ ንሜቻ ደግሞ በኤቨርተን ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሯል። በዛሬው ጨዋታ ሊድስ ማሸነፍ ከቻለ በመጀመርያዎቹ ሁለት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከ2002/2003 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ የቻለ በሚል ለራሱ ታሪክ ይጽፋል። ሊድስ በለንደን ባደረጋቸው ያለፉ 30 ጨዋታዎች 23 ጊዜ ተሸንፏል። ጨዋታውም 1፡30 ላይ ይካሄዳል። ሌሎች 11:00 ላይ በርንማውዝ ከዎልቨስ፣ ብሬንትፎርድ ከአስቶንቪላ፣ እና በርንሌይ ከሰንደርላንድ ሌሎች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን