ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በናይጀሪያዋ ከተማ አቡኩታ ነገ ይጀመራል፡፡
ከ43 ሀገራት የተወጣጡ ከ930 በላይ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ፉክክራቸውን ያደርጋሉ፡፡
ከ20 ዓመት በታች 13 መድረኮችን ከ18 ዓመት በታች ደግሞ ሁለት ውድድሮችን ከዚህ ቀደም አከናውነዋል፡፡ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የበላይ መሪነት የሚከናወነው ውድድሩ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
ከኮትዲቯሯ አቢጃን እና ከዛምቢያዋ ንዶላ በመቀጠል የናይጀሪያዋ ከተማ አቡኩታ በአቢዮላ ስታዲየም የመክፈቻ ሥነ ሥርአቱን ታከናውናለች፡፡
በዚህ ስታዲየም ውድድሩ ሲጀመርም የአፍሪካ የወደፊት የአትሌቲክስ ኮከቦች በአንድነት ይሰየማሉ።
በአትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምን መጻፍ የቻሉ አትሌቶችን በማፍራት የሚታወቁት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ሞሮኮ ተጠባቂዎች ናቸው።
ዩጋንዳ፣ ቦትስዋና፣ ካሜሩን እና ሴኔጋልም ተፎካካሪ በመኾን ለውድድሩ ድምቀት እንደሚኾኑ ተጠብቋል።
የመጀመሪያው ቀን ከ18 ዓመት በታች ተወዳዳሪዎች በየዘርፎቻቸው በሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
ከ100 ሜትር ማጣሪያ እስከ 1500 ሜትር ፍጻሜ ድረስ ይካሄዳሉ።
በእድሜ ምርመራ ውዝግብ ውስጥ ሆኖ አቡኩታ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ልኡክ 68 አባላትን ይዟል፡፡ 18ቱም ተወዳዳሪ ናቸው፡፡
የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀነሰ ቢመጣም እንደ ድርቤ ወልተጂ፣ ዘርፌ ወንድማገኝ እና ለሜቻ ግርማን የመሳሰሉ አትሌቶች የተገኙበት ውድደር ነው፡፡ አይናዲስ መብራቱ እና ምስጋና ዋቁማም ተጠቃሾች ናቸው።
ኢትጵያውያን አትሌቶች በ16 ዘርፎች ይካፈላሉ፡፡ ከ18 ዓመት በታች በስምንት በተመሳሳይ ከ20 ዓመት በታች በስምንት የማጣሪያ እና የፍጻሜ ፍልሚያዎችን ያደርጋሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉባቸው ውድድሮች ነገ 11:00 ላይ ይጀምራሉ፡፡ ከ18 ዓመት በታች ወንዶች ከፍታ ዝላይ ማጣሪያ ነው፡፡ በዚህ መደብ ንያጆክ ቾል ብቸኛው ተሳታፊ ነው፡፡
የ100 ሜትር ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የወንድና የሴት ማጣሪያም ቀጥሎ ይካሄዳል። በወንድ ከ20 ዓመት በታችም መብራት ካሳ ብቸኛ ተሳታፊ ነው።
በሴት ከ18 ዓመት በታች ሲንቦኔ ተስፋ ትሳተፋለች። ከ20 ዓመት በታች ደግሞ ሁለቱ ወጣት አትሌቶች ሰላማዊት ኮከብ እና ደሚቱ ሺፈራው ማጣሪያቸውን ያደርጋሉ፡፡ የሴቶቹ የሚጀምረው 12: 05 ሲል ነው፡፡
የ1500 ሜትር የሁለቱም ጾታ ከ18 ዓመት በታች ፍጻሜ ውድድር ይጠበቃል፡፡ 12: 35 ሲል ሲጀምር በሴቶቹ ኤልሳቤት አማረ፣ ደስታ ታደሰ እና ቦንቱ ዳንኤል ለሜዳልያ ይፋለማሉ፡፡
ከደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማእከል የተገኘችው እና የአኹኗ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌት ደስታ ታደሰ በርቀቱ ትጠበቃለች፡፡
ኢትጵያውያን አትሌቶች በ2023 ንዶላ ላይ በዚህ ርቀት ከ20 ዓመት በታች ከአንድ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ሁሉንም ሜዳልያ ማግኘታቸው ይታወሳል። ከ18 ዓመት በታቹ ላይ አሰለፍ አማረ የነሃስ ሜዳልያን አስገኝታ ነበር፡፡
በወንዶቹ ከ18 ዓመት በታች ሳሙኤል ገብረ ሃዋርያ እና አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር ይጠበቃሉ፡፡ ውድድሩ ምሽት 12: 45 ላይ ይደረጋል፡፡
ከምሽት 1: 05 ጀምሮ የ400 ሜትር ማጣሪያ በሁለቱም የእድሜ እርከን በሴቶቹ እዲደረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡
ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ባንችአምላክ ባይክስ እና ገነት አየለ ሲሳተፉ በ20 ዓመት በታች ደግሞ አጃይባ አሊዬ ብቸኛ ተወዳዳሪ ናት፡፡ ይኹኔ ዘመኑ በወንዶቹ ከ18 ዓመት በታች 400 ሜትር ላይ ይሳተፋል፡፡
ምሽት ላይ ኢትዮጵያ ለሌላ ሜዳልያ የምትጠብቅባቸው ሁለት ርቀቶች የፍጻሜ ውድድሮች ይከናወናሉ፡፡ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች 3 ሺህ ሜትር እና 10 ሺህ ሜትር እርምጃ ፍጻሜዎች ተጠባቂ ናቸው።
ቀድሞ የሚደረገው የ3ሺህ ሜትር ፍጻሜ ሲሆን ምሽት 2 :25 ሲል ይጀምራል፡፡ ቤተልሄም ጥላሁን እና ትርሃስ ገብረሕይወት ቀድመው የመጨረሻ መሙን ለማቋረጥ ይሮጣሉ፡፡
ኢትዮጵያ በ2019 በአቢጃንም ይሁን በ2023 ንዶላ በርቀቱ 5 ሜዳልያዎችን አሳክታለች፡፡ በተለይ በ2023 የዛምቢያ ንዶላ መድረክ የአረንጓዴው ጎርፍ ከታየባቸው ሦስት ርቀቶች መካከል ከ20 ዓመት በታች የሴቶች 3ሺህ ሜትር አንደኛው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ የሚከናወነው ከ20 ዓመት በታች ሴት የ10 ሺህ ሜትር እርምጃ ውድድር ነው፡፡ ብርሃን ሙሉ ብቸኛ ተወዳዳሪ ናት፡፡
በአቢጃኑ የመጀመሪያ ውድድር ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ በ10 ብር እና በ14 ነሃስ በድምሩ በ30 ሜዳልያ አምስተኛ ኾና ነው ያጠናቀቀችው።
ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረገው የንዶላው መድረክ ደግሞ 4 ወርቅ፣ 7 ብር እና 4 ነሃስ ጠቅላላ 15 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው።
ዘጋቢ:- ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን