በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ፋሲል ከተማ ከመቻል ወሳኝ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።

0
298

ባሕርዳር: ጥር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ በ12ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል።ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከመቻል ምሽት 12 ሰዓት ይጫዎታሉ።

ፋሲል ከተማ በሊጉ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስቱን ጨዋታዎች አሸንፎ ፣ በሦስቱ አቻ ወጥቶ ፣ በሦስቱ ተሸንፎ እና በስድስት የግብ ክፍያ በ18 ነጥብ ደረጃው አምስተኛ ነው፡፡
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘው ፋሲል ከተማ ለወራት ወጥ አቋም ለመያዝ ሲቸገር ተስተውሏል፡፡

በፋሲል ከነማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ኢዮብ ማቲያስ እና ፍቃዱ አለሙ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ኾኗል፡፡ የመስመር ተከላካዩ ዓለምብርሀን ይግዛው ደግሞ በቅጣት ከጨዋታ ውጭ ነው።

መቻል በበኩሉ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንቱ አሸንፎ፣በሁለቱ አቻ ወጥቶ ፣ በአንዱ ተሸንፎ በዘጠኝ የግብ ክፍያ እና በ26 ነጥብ ደረጃው ሁለተኛ ነው፡፡

ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አስደናቂ ጨዋታ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ የቡድኑ የመሐል ክፍሉ ኳስን አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ በግብ ላይ የተሻለ ተሳትፎን እያደረገ ይገኛል፡፡
ስለኾነም ቡድኑ በጥሩ አቋም የሚገኝ በመኾኑ ዛሬ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመቻል በኩል ሙሉ ስብስቡ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ መኾኑ ተረጋግጧል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከተማ ስድስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ መቻል ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በዋና ዳኝነት ይመሩታል፡፡

ቀን 9 ሰዓት በሚደረግ ጨዋታ በሊጉ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ ጋር ይጫወታሉ፡፡

ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ26 ነጥብ እና በ13 የግብ ክፍያ ይመረዋል፡፡ መቻል በ26 ነጥብ እና በ9 የግብ ክፍያ በሁለተኛነት ተቀምጧል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ21 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here