አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ የቦክስ ክለቦች ውድድር ተጠናቀቀ።

0
81

ጎንደር፡ ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ውድድር መርሐግብር ከሐምሌ 4/2017 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ ቆይቷል።

ዛሬ የመዝጊያ ጨዋታው የተለያዩ የቦክስ ስፖርት አፍቃሪን እና የስፖርት መሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

የፍጻሜው ጨዋታ በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታዎች 12 የቦክስ የውድድር ዘርፎችን ያቀፈ ነው። በውድድሩ አሸናፊ የኾኑ ስፖርተኞች የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዛሬው የመዝጊያ መርሐግብር ላይ ከተካሄዱ ውድድሮች ውስጥ በ48 ኪሎ ግራም የፋሲል ከነማው አብራው ፈንታ ከድሬዳዋው ቢኒያም ፍቅሩ ጋር ተገናኝተው አብራራው ፈንታ አሸንፏል።

በወንዶች በ54 ኪሎግራም የፋሲል ከነማው መልካሙ ውቤ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከሀብታሙ ዘሪሁን ጋር ባደረጉት ጨዋታ መልካሙ ውቤ አሸንፏል።

በ75 ኪሎግራም የፋሲል ከነማው አንዳርጋቸው ገብረ መድህን ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ይታገሱ ፍቃዱ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አንዳርጋቸው ገብረ መድህን ማሸነፍ ችሏል።

በወንዶች በ80 ኪሎግራም የፋሲል ከነማው ገብረ ሚካኤል መካሻው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን ማሞ ሞሲሳን በማሸነፍ የወርቅ ዋንጫ አንስቷል።

በወንዶች የዓመቱ ኮከብ ቦክሰኛ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አብርሃም ዓለም ሲመረጥ የድሬዳዋ ከተማዋ ወርቅነሽ ዋቅጅራ በሴቶች የዓመቱ ኮከብ ቦክሰኛ ኾና ተመርጣለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦክስ ፌዴሬሽን በዓመቱ ባደረጋቸው የቦክስ ክለቦች ውድድር አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በወንዶች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ ኾነዋል። በዓመቱ አጠቃላይ አሸናፊ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የቦክስ ክለብ ኾኖ የወርቅ ዋንጫ ተሸላሚ ኾኗል።

የፋሲል ከነማ የቦክስ ክለብ ደግሞ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ መኾኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስንታየሁ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦክስ ክለቦች የቦክስ ፌዴሬሽን በተያዘው ዓመት ሦሥት የቦክስ ውድድሮችን በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ የተካሄደው የመጨረሻው ዙር የፌዴሬሽኑ መርሐግብር መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here