ባሕር ዳር ፡ ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ ወጣቶችና ስፓርት መምሪያ ከአማራ ልማት ማኅበር ጋር በመተባበር ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የአልማ ሳምንት ምክንያት በማድረግ “ለአልማ እሮጣለሁ ማኅበራዊ ኃላፊነቴን እወጣለሁ ” በሚል መሪ መልዕክት የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በውድድሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ልማት ማኅበር ሥትራቴጅ እና ኢኖቬሽን ምክትል ሥራ አሥፈፃሚ አበረ መኩሪያ የአማራ ልማት ማኅበር የልማትና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጭ ፕሮጀክቶችን ከሕዝቡ እና ከአጋር አካላት በሚያገኘው ሀብት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የተገኘውን ሀብት ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ ሥራ ላይ እያዋሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአልማ ሳምንት በየዓመቱ ከሐምሌ 1 እስከ 15 ይከበራል። የአልማን ሳምንት የችግኝ ተከላ ፣ ደም ልገሳ እና ሕዝባዊ ስፓርታዊ ውድድሮችን በማካሄድ እያከበሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የዘንድሮው የአልማ ሳምንት ለአምስተኛ ጊዜ እየተከበረ መኾኑን አንስተዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳድር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ከተማዋ በኮሪደር ልማት በደመቀችበት ውብና ማራኪ በኾነችበት ወቅት ስፓርታዊ ውድድር ማካሄድ ልዩ ድምቀት መኾኑን ተናግረዋል።
የከተማዋ ዘርፈ ብዙ ልማት ወጣቶችን ጠቃሚ ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም በባሕርዳር ከተማ ስፓርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን