ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በዚያ የጭንቅ ጊዜ ብዙዎች አልፈዋል። በጥይት አረር እየተቀሰፉ ወድቀዋል። ላይመለሱ አንቀላፍተዋል። ላይነቁ ተኝተዋል። በዚያ ጊዜ ብዙ ሕልሞች በጥይት ተበልተዋል። ብዙ ራዕዮች በቦንብ አረር ተነጥቀዋል።
ብዙ ምኞቶች እንደዘበት ቀርተዋል። እልፍ አዕላፍ ተስፋዎች እንደ ጉም ተነው፣ እንደ ጭስ በነው ጠፍተዋል፡፡ በዚያ ዘመን አያሌ እናቶች መሪር ሀዘን አዝነዋል። መሪር ለቅሶ አልቅሰዋል።
ከግራ ቀኝ የሚተኮሱ ጥይቶች፣ ከፊት ከኋላ የሚያጓሩ ቦንቦች ነፍሳቸውን ለማትረፍ ወዲያ ወዲህ የሚቅበዘበዙትን ንጹሐንን በልተዋል። ድንገት እንዳልነበር አድርገው አስቀርተዋል።
የቤተሰብን ደስታ ነጥቀዋል። እናት እና ልጅን ነጣጥለዋል። የደመቁ ከተሞችን አፈራርሰዋል፡፡ የተዋቡ ጎዳናዎችን ጭር አድርገዋል፡፡
ጦርነት ክፉ ነው ደረቁንም እርጥቡንም ይበላል። ንፁሁንም ወንጀለኛውንም ይወስዳል። ታናሹንም ታላቁንም ይቀስፋል። አያሌ ሕልሞችን ቀጭቶ ምድርን ምድረ በዳ ያደርጋል።
በጦርነት የትውልድ አበባዎች ይረግፋሉ። ለፍሬ የደረሱትም ጥቅም ሳይሰጡ ይወድቃሉ። የሚመርቁ እና ታሪክ የሚነግሩ አረጋውያን ታሪክ እንደያዙ፣ ለልጅ ልጅ ሳይነግሩት ያልፋሉ።
ጦርነት ዘመንን፣ ሕይወትን፣ ንብረትን፣ ሕልምን እና ራዕይን በአንድ ጊዜ ይነጥቃል፡፡ የጦርነት ትርፉ ሞት እና ጸጸት ነው፡፡ ለወትሮው ወንድማማቾች የነበሩ ጎራ ለይተው የተዋደቁበት፣ ምሽግ ቆፍረው የተታኮሱበት፣ አንድነት አያሻንም ብለው ተነጣጥለው ለመኖር የተፋለሙበት የባልካን ጦርነት ብዙዎችን በልቷል።
የባልካን ጦርነት በዘመኑ ታላቅ የሶሻሊስት ሀገር የነበረችውን ዩጎዝላቪያን አፈራርሷል፡፡ በአንዲት ሠንደቅ ሥር የነበሩ ዜጎችን እንደ ጠላት አለያይቷል፡፡ ዮጎዝላቪያውያን በአንድ ላይ ኾነው ታላቅ ሳሉ ተከፋፍለው ታናናሾች ኾነዋል፡፡
በአንድነታቸው ሳሉ ብዙዎች የዩጎዝላቪያን የሾሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ቀድተው ወስደዋል፡፡ ተሞክሮዎችን ሁሉ ከዩጎዝላቪያ እየቀዱ ወደሀገራቸው ተጉዘዋል፡፡ ከባልካን ጦርነት ማግሥት ግን ያቺ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም መቅጃ ምንጭ የነበረች ሀገር አርያነቷ ቀርቶ የፈረሰች፣ የተገረሰሰች፣ ታላቅ ሳለች የታናናሾች ሀገር ኾነች፡፡
ቢቢሲ በዘገባው የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በመራራ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጠረች የሶሻሊስት ሀገር ነበረች ይላል፡፡ ያቺ በፌደፈዴሬሽን የምትተዳደር ሀገር ዜጎቿ በጥሩ ደረጃ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ በፕሬዝዳንት ቲቶ መሪነት በዩጎዝላቪያውያን መካከል የነበረው ውጥረት በተሳካ ሁኔታ ተወግዶ ሀገሪቱ በጥሩ ኹኔታ ላይም ነበረች፡፡ ይህ ግን ዘላቂ አልነበረም፡፡
እ.ኤ.አ. በ1980 ፕሬዝዳንት ቲቶ ሲሞቱ በዩጎዝላቪያውያን የነበረው መጠራጠር እንደገና ተፈጠረ ይላል ቢቢሲ፡፡ የብሔርተኝነት አስተሳሰቦች ተቀነቀኑ፡፡ ብሔርተኞች ብሔርተኝነትን አቀነቀኑ፡፡ ወጠሩት፣ አከረሩት፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግም ሊያረግቡት አልተቻላቸውም፡፡ ውጥረቱ ከውጥረት ተሻገረና ጦር አማዘዘ፡፡ በአንድ ፕሬዝዳንት፣ በአንዲት ሠንደቅ ዓላማ ሲተዳደሩ የነበሩ ወገኖች ጎራ ለይተው ተጋደሉ፡፡ ብዙዎች አለቁ፡፡
ሕጻናት ሮጠው ሳይጠግቡ ረገፉ፡፡
ሕጻናት ከቀኝ ከግራ፣ ከፊት ከኋላ በሚተኮሱ ጥይቶች እየተመቱ የሚያልፉ ሰዎችን በልጅነት ዘመናቸው ተመለከቱ፡፡
በዚህ ዘመን ለታላቅነት የተዘጋጀ ከሞቱት የተረፈ። በሕይወት ኾነው ከሚሰቃዩ፣ ክፉውን ሁሉ በዓይናቸው ከተመለከቱ ሕጻናት መካከል አንድ ሉካ የተሰኘ ሕጻን ነበር።
ተባብረው ሀገራቸውን ለማፍረስ በሚታኮሱ ዮጎዝላቪያውያን የሚወድቁ ሰዎችን ተመልክቷል፡፡ የቅርብ ዘመዶቹን በጦርነት አጥቷል፡፡ እርሱም የትኛዋ ጥይት ከገላዬ ላይ ተሰክታ ትጥለኝ ይኾን እያለ በልጅነት አቅሙ በፍርሃት ተንጧል፡፡ ” ቅጠል ያለቀኗ አትበጠስም ” እንዳለ የሀገሬ ሰው የሉካ ነፍስ መበጠሻ ጊዜ ገና ነበረችና ከመቅሰፍቱ ተረፈ።
በሰማይ በምድሩ የሚያጓሩ የጥይት እና የቦንብ ድምጾች አልፈውታል። ከፊት ከኋላው፣ ከግራ ከቀኙ ከሚሰሙ ጥይቶች ሾልኳል። የባልካን ጦርነት የሞት መልዕክተኞች አላገኙትም። ነፍሱንም አልያዟትም።
ዩጎዝላቪያውያን ሀገራቸውን በማፍረስ የሚሸለሙ ይመስል በሽቅድድም አፈረሷት፡፡ በዚያ አስከፊ የባልካን ጦርነት ብዙዎች ተሰደዱ፡፡ ቀያቸውን እየጣሉ ነፍስ አውጭኝ እግራቸው ወደ መራቸው ተጓዙ፡፡ ሉካም ከእነዚያ የሞት መልዕክተኛ በከበባቸው ሰዎች መካከል ነበር፡፡
ሉካ ሞድሪች እ.አ.እ መስከረም 9/1985 በክሮሺያ ዛዳር ነበር የተወለደው፡፡ አስ የሞድሪችን ታሪክ በቀመረበት መዝገቡ ዛሬ በታሪክ ከታዩ ምርጥ ተጨዋቾች መካከል አንደኛው እ.አ.አ በ2018 የባላንዶር አሸናፊው ሞድሪች ከዚህ ከመድረሱ በፊት አያሌ መከራዎችን አሳልፏል ይላል፡፡ እርሱ በሕይወት ውስጥ እግር ኳስን ብቻ አይደለም ያሸነፈው ጦርነትን እና አትችልም መባልን ጨምር እንጂ፡፡
ከጦርነት አረር ተርፎ የነፍሱ ጥሪ ወደ ኾነች እግር ኳስ በሄደ ጊዜ አንተ ለእግር ኳስ አልተፈጠርክም፣ አትችልም ተብሎ ተመልሷል፡፡
ነገር ግን ከጦርነት የተረፈው ሉካ አትችልም የሚለውን አምኖ አልተቀበለም፡፡ ይልቅስ በርትቶ ሠርቶ ችሎታውን በዓለም ላይ አስመሰከረ እንጂ፡፡
ሉካ በጥረቱ በዓለም ላይ ነገሠ፡፡ ዓለም የባልካን ጦርነት ስንቱን ሕጻናት አሳጣን እያለ፣ ጦርነት ያሳጣውን እያሰበ እንዲቆጭ አደረገ፡፡ ሉካ የልጅነት ጊዜውን ስቃይ በከበባት ተስፋ አሳለፈ።
ደም አፋሳሹ የባልካን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የሞድሪች ቤተሰቦች 60 ኪሎ ሜትሮችም ርቀው መጓዝ ነበረባቸው። በዚያ ጦርነት ከቀየው የራቀው ሉካ በዛዳር አካባቢ ባሉ ሆቴሎች ውስጥ በስደተኛነት ይኖር ነበር። እዚያም በሆቴሎች የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ውስጥ እግር ኳስ መጫወት ጀመረ፡፡
ሉካ በቦምብ እና በሳይረን ድምጽ መካከል አሳዛኝ ክስተት ተመልክቷል። አያቱ ዓይኑ እያየ ሲገደሉ አይቷልና፡፡ ከሞት የተረፉት ቤተሰቦቹ ላለመሞት በጫካ እና በተራራዎች ከመሸሽ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ያ ቀጫጫ ተስፈኛ በየቀኑ የቦንብ እና የጥይት ድምጽ ቢሰማም አንድ ቀን ከፍ ባለ ደረጃ እግር ኳስ እንደሚጫወት ለራሱ ይነግረው ነበር፡፡
ሉካ በስምንት ዓመቱ ሕልሜ ወደሚለው ሀይዱክ ክለብ ገብቶ ለመጫወት ተስፋ ሰነቀ፡፡ በስምንት ዓመቱ ለሕልሙ ክለብ ለመጫወት ያደረገው ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀረ፡፡ ቀጫጫ እና አጭር ነበርና አትኾንም ተብሎ ተመለሰ፡፡ ሉካ ግን ተስፋ ቆርጦ እግር ኳስን ለመተው አልወሰነም፡፡ ይልቅስ በርትቶ ሠራ፡፡ ሰዎች ከሕልሙ ያርቁታል፡፡ እርሱ ግን በርትቶ እየሠራ ወደ ሕልሙ ይጠጋል፡፡ ለዛውም የባልካንን አስከፊ የጦርነት ትዝታዎች እያስታወሰ ነበር ለሕልሙ በርትቶ የሚሠራው፡፡
ሉካ በማድሪድ እያለ ስለዚያ የልጅነት ዘመኑ ሲናገር እንዲህ ይላል። የልጅነት ጊዜዎቼ በጣም በስቃይ የተሞሉ ነበሩ። ያ ጦርነት ሲጀመር ገና አመስት ዓመቴ ነበር። በጦርነት ቀጣና ውስጥ እየኖርኩ አያቴን በጦርነት አጣሁ።
እኛ በስደተኞች መጠለያ እንድንኖር ተገደናል። በዛ ላይ በአቅራቢያው የጥይት እና የቦንብ ድምጽ ይሰማል። ግድያዎችም ብዙዎች ነበሩ። ጦርነቱ እንዳበቃ እግር ኳስ መጫወት ጀመርኩ።
የምወደው ክለብ ሀይዱክ የመጫወት ዕድል ይሰጠኛል ብዬ ስጠብቅ በጣም ትንሽ፣ ክብደቴ ቀላል እና ቀጫጫ ነበርኩና ይህን ልጅ አላጫውትም ብሎ መለሰኝ።
አባቴ ግን መከረኝ። ልጄ ዛሬ ያላመኑብህን እንዲያምኑ ማድረግ ትችላለህ አለኝ። እግርኳስን ተስፋ ቆርጬ አላቆምኩም። በአጨዋወት ስልቴ ላይ ብዙ ሰርቻለሁ። ከዚያም በሀገሬ ክሮሺያ የመጫወት ዕድል አገኘሁ። ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሄጄ ለቶተንሃም ፊርማዬን አኖርኩ። ነገር ግን ብዙዎች ሉካ በእንግሊዝ መጫወት አይችልም አሉ።
እኔ ግን እንደምጫወት አሳየሁ። በእንግሊዝ መጫወት አይችልም ያሉኝን እንደ ተሳሳቱ አረጋግጨላቸዋለሁ። አሁን ደግሞ ለዓለም ትልቁ ክለብ ሪያል ማድሪድ እየተጫወትኩ መኾኔን በኩራት እናገራለሁ ነበር ያለው።
በስምንት ዓመቱ አትሆንም የተባለው ብላቴና በ16 ዓመቱ በክሮሺያ ታላቁ ለኾነው ክለብ ዳይናሞዛግሬብ ፈረመ፡፡ ሉካ የሕልሙን ገመድ አጥብቆ ጨበጠው፡፡
ሉካ በዳይናሞዛግሬብ እንደደረሰ ስኬታማ አልኾነም፡፡ በውሰት ተሰጥቶ ተጫውቷል፡፡ ሥራውን ጠንክሮ ሠራ፡፡ ሕልሙን ተከተለ፡፡ ሞድሪች ወደ ዳይናሞዛግሬብ ተመልሶ መጫወት ጀመረ፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በ73 ጨዋታዎች 22 ግቦችን አስቆጠረ፡፡ 21 ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀበለ፡፡ በመሐል ሜዳው እንደ ሸረሪት እንደ አሻው ሲሽከረከር ያዩት ሁሉ የሞድሪችን ቅጥነት እና የቁመት ማጠር ረሱት፡፡ በብቃቱ ተደነቁ፡፡ ተገረሙ፡፡
ድንቅ ብቃት አሳይቷልና ማንም ሰው ስለ ቀጫጫነቱ አላነሳም፡፡ ይልቅስ ወሬው ሁሉ ስለ ብቃቱ ኾነ፡፡
ሉካ ያን ዘመን ሲያስታውስ “እኔ ራሴን ፈጽሞ አልተጠራጠርኩትም ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ሁልጊዜ እዚህ መድረስ እንደምችል አስብ ነበር፡፡ ፈጣሪ ይመስገን እውነት ነው። ያ አትችልም የሚለው እንቅፋት አልነበረም፣ ነገር ግን ለእኔ ተጨማሪ ተነሳሽነት ነበር እንጂ። እግር ኳስ ለመጫወት ብርቱ መኾን አያስፈልግም” ይላል፡፡ ለእግር ኳስ ወፍራም እና ረጅም መኾን ሳይኾን የአዕምሮ ብስለት እንደሚያስፈልግ ሲናገር።
ሉካ እ.ኤ.አ. በ2008 በእንግሊዙ ክለብ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ዕይታ ውስጥ ገባ፡፡ በ20 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ለንደን አቀና፡፡ የሞደሪች የእግር ኳስ ሕይወት የበለጠ መስመር ያዘ፡፡ ሉካ ወደ ሕልሙ ቀረበ፡፡ በነጩ መለያ ተፍለቅላቂው አማካይ አስደናቂ ብቃቱን አሳዬ፡፡ ለዓመታት በቶተንሃም ቤት በግሩም ብቃት ታየ።
ያን ጊዜ የዓለም ከዋክብትን የሚያነፈንፈው ሪያል ማድሪድ ከዓመታት በፊት አትችልም ተብሎ የተገፋውን ኮኮብ ተመለከተው፡፡በ2012 በ30 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ ወደ ስፔን አስኮበለለው፡፡ አሁን በዓለም ላይ ኀያል ለኾነው ክለብ ፈርሟል፡፡ የሕልሙ ገመድ ጎትቶ ወደ ትክክለኛው ቦታ አድርሶታል።
ተስፋ እና ጠንካራ ሥራው ከሕልሙ ቤት አደረሰው፡፡ አስ የሉካን ታሪክ በመዘገበበት መዝገቡ ያ መልካም ልጅ በማድሪድ ቤት በመጀመሪያው ዓመት የማይገባው ዋጋ ወጥቶበታል ተብሎ ተተችቶ ነበር ይላል፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የብቃት ጣሪያውን እያሳደገ በማድሪድ ቁልፉ ተጨዋች ኾነ፡፡ በዓለም ላይም አስደናቂው ኮኮብ ተሰኘ፡፡ በማድሪድ በዋንጫ ያሸበረቀ ተጫዋችም ኾነ፡፡
ሉካ ከዩጎዝላቪያ ተከፍላ ብቻዋን ሀገር ለኾነችው ክሮሺያ በእግር ኳስ ምልክቷ ኾናት፡፡ በ2018 የዓለም ዋንጫ አስደናቂ ብቃቱን አሳይቶ ሀገሩን ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አበቃ፡፡ ምንም እንኳን በፈረንሳይ ተሸንፈው ዋንጫውን ወደ ክሮሺያ መውሰድ ባይቻለውም በዓለም ዋንጫው ባሳየው ድንቅ ብቃት ተደነቀ፡፡ በክሮሺያ እንደ ብሔራዊ ጀግና ተቆጠረ፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት እንደ ጀግና ሸለመው።
ባሳየው ጀብዱም የ2018 የባላንዶር አሸናፊ ተሰኘ፡፡ ከዓመታት በፊት በሕልሙ ክለብ ሀይዱክ አትችልም ተብሎ የተሰናበተው ሉካ ተስፋ ሳይቆርጥ ባሳዬው ጽናት በዓለማችን ኀያሉ ክለብ ተጫውቶ የዓለም ኮኮብ ተሰኘ፡፡ ከባልካን ጦርነት የተረፈች ነፍስ የዓለም ኮኮብ ተሰኘች፡፡
የባልካን ጦርነት እንደ ቀጠፋቸው ሕጻናት ሁሉ ከንፈር በመምጠጥ ትታለፍ የነበረች ነፍስ በታምር ተርፋ አስደናቂ ጥበብ አሳየች፡፡ ለዓለም እግር ኳስም እንደ ስጦታ ተሰጠች፡፡
አስ እንዲህ ይላል “ያ ትንሹ ሉካ በጦርነቱ መካከል በሆቴል የመኪና መቋሚያ ውስጥ የተጫወተው፣ አያቱ ሲሞቱ ያየው፣ በአካለ ቀጫጫነቱ ምክንያት በሕልሙ ክለብ መጫወት ውድቅ የተደረገበት፣ የዓለማችን ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ይታወቃል። ፈገግታው እና ሕልሙ አልጠፋም፡፡ እናም የእግር ኳስ ዓለም ስሙን እና የእሱን ቆንጆ የማሸነፍ ታሪክ ያስታውሳል፡፡
ከክሮሺያ ዛዳር ተነስቶ፣
በዳይናሞ ዛግሬብ አጉጦ፣ በእንግሊዝ በቶተንሃም ቤት አብቦ፣ በስፔን ማድሪድ ያፈራው ሉካ ከ13 ዓመታት የማድሪድ የልዕልና ዘመን በኋላ ተለያይቷል፡፡
በማድሪድ ቤት በወርቅ ቀለም የጻፈው የእግር ኳስ ዘመኑ ምዕራፍ ተዘግቷል፡፡ ከእንግዲህ የሚከፈተው ለመነበብ ብቻ ነው፡፡ በ28 ዋንጫዎች አጊጦ ማድሪድን በልቡ ውስጥ አትሞ ወደ ጣሊያን አቅንቷል፡፡ በቅንጡዋ የጣሊያን ከተማ ሚላን፣ ለታሪካዊው ክለብ ኤሲ ሚላን ፈርሟል፡፡
ሉካ ከማድሪድ ጋር መለያየቱን ባወቀ ጊዜ “ጊዜው ደርሷል፤ ይህ እግር ኳስ ነው፣ እናም በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር መጀመሪያ እና መጨረሻ አለው” አለ፡፡ መጨረሻው ደረሰና አያሌ ታሪክ ከሠራበት ማድሪድ ጋር መለያየት ግድ ኾነበት።
ለሪያል ማድሪድ መጫወቴ እንደ እግር ኳስ ተጫዋች እና እንደ ሰው ህይወቴን ለውጦታል የሚለው ሉካ በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ስኬታማ በኾነው ክለብ ውስጥ የታሪክ አካል በመኾኔ እኮራለሁ ብሏል፡፡
ቢቢሲ የሉካ ሞድሪች የእግር ኳስ አሻራ ለዘለዓለም ይኖራል ይላል፡፡ የሪያል ማድሪዱ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንትኖ ፔሬዝ ስለ ሞድሪች ሲናገሩ ሞድሪች በሁሉም የማድሪድ ቤተሰቦች ልብ ውስጥ እንደ ልዩ እና አርዓያነት ያለው የእግር ኳስ ተጨዋች ኾኖ ይኖራል ብለዋል።
የዛዳሩ ብላቴና፣ ቀጫጫነቱ ያስገፋው ተስፈኛ አሁን ነጩን መለያ አውልቆ በቀይ እና ጥቁር ያሸበረቀውን መለያ ሊለብስ ወደጣሊያን ተጉዟል።
በጣሊያን ምን ያሳይ ይኾን? የሚለው ይጠበቃል። አትችልምን እና ጦርነትን በአንድ ወቅት ያሸነፈው ሉካ የፈተና ዘመኑ፣ የድል ታሪኩ፣ የይቻላል መንፈሱ ታዳጊዎችን እንዳስተማረ ይኖራል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን