በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

0
88

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ34ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሕር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታል። በደረጃ ሠንጠረዡ በ48 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ጊዜያት ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን አቻ ተለያይተው ሦስቱን በሽንፈት መጨረሳቸው ቡድኑ ደካማ አቋም ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡

የጣና ሞገዶቹ ውጤት ከመራቅም ባለፈ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ግብ በማስቆጠርም በኩል ያላቸው አቋም ደካማ ኾኖ ተስተውሏል። ባደረጓቸው ጨዋታዎችም ግብ ማስቆጠር የቻሉት አንድ ብቻ መኾኑ ደግሞ አሠልጣኙ በዛሬው ጨዋታ ለውጥ ማድረግ ካልቻሉ የያዙትን ደረጃ ለቀው መንሸራተታቸው አይቀሬ ይኾናል፡፡

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። የአጥቂው ክፍልም ቢኾን ከዚህ በፊት በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ቢኾንም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን አንድ ግብ ብቻ ነው ያስቆጠረው። ይህ ቡድኑ በማጥቃትም ኾነ በመከላከል ረገድ መድከሙን ያሳያል። የጣና ሞገዶቹ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋ የግድ የሚላቸው ያሉበትን የሦስተኛ ደረጃ ላለማጣት ነው።

ወጥ አቋም የሌለው ተጋጣሚው ወላይታ ዲቻ ባለፈው ፋሲል ከነማን 3ለ0 መርታቱ ቡድኑ ቀደም ብሎ ካደረጋቸው የሦስት ጊዜ ሽንፈት እና የአንድ ጊዜ አቻ ጨዋታ በተወሰነም ቢኾን መሻሻል ማሳየቱን አመላካች ነው፡፡ ወላይታ ዲቻዎች በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ በ45 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ነው የተቀመጡት፡፡

ባሕር ዳር ከተማ እና ወላይታ ዲቻ ከዚህ ቀደም 12 ጊዜ ተገናኝተዋል። የጣና ሞገዶቹ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ ወላይታ ዲቻ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ሰባት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታውም ምሽት 12፡00 ላይ ይካሄዳል።

ሲዳማ ቡና ከድሬ ዳዋ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ቀን 9፡00 የሚካሄድ የዛሬ ሌላኛው ጨዋታ ነው።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here