ደባርቅ: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ስፖርት ጽሕፈት ቤት ላለፉት ዘጠኝ ወራት “ስፖርት ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የበጋ ስፖርታዊ ውድድር ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል። በዓመቱ “ስፖርት ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች 86 ቡድኖች የተሳተፉበት የበጋ ስፖርታዊ ውድድር በማካሄድ ወጣቶችን የማብቃት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ልዑል መስፍን ስፖርት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶች ያላቸውን ስፖርታዊ ክህሎት እንዲያሳድጉ እና ነገ የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል ስፖርታዊ ውድድሩ የሚበረታታ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አሥተዳደሩም የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶችን በመሥራት እና ቁሳቁሶችን በማሟላት ዘርፉን እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን የይዞታ ባለቤትነት በማስከበር ወጣቶቹ ስፖርታዊ ተሰጧቸውን የሚያሳድጉበት ቦታ በየአካባቢው እንዲኖር ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም ወጣቶች ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ስፖርታዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስጦታው ታጀበ ውድድሩ ከመስከረም 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱ አስታውሰዋል፡፡
በውድድሩም የተሻለ ብቃት የነበራቸውን ወጣቶች በመመልመል በክልል አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ስፖርት ለጤና፣ ለማኅበራዊ ህይዎት ትስስር፣ ለተዝናኖት እና ለሰላም ያለው አስተዋጾኦ ከፍ ያለ በመኾኑ ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ከተለያዩ የስፖርት ክለቦች ጋር በመነጋገር ወጣቶችን የማስመልመል እና ስፖርታዊ ተሰጧቸው እንዲያሳዩ እድል የመፍጠር ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ወቅታዊ የሰላም ኹኔታ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ፈታኝ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይኹን እንጂ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን በመቅረፍ ውድድሩን ለማስቀጠል ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ውድድሩን ከቡድን ወደ ሊግ ውድድር በማሸጋገር የስፖርቱን እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በውድድሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተጫዋቾችም በበኩላቸው ውድድሩ ስፖርታዊ ተሰጥኦን ለማሳየት እና ወደ ተለያዩ ክለቦች ለመዘዋወር የሚያስችል እድል እንደፈጠረላቸው አንስተዋል፡፡
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን ወክሎ ሲጫወት የነበረው ዎርቦል ዊኝዋንስ በውድድሩ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጾ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡ ስፖርታዊ ውድድሩ ለወጣቶች የጤና፣ ማኅበራዊ እና ተዝናኖታዊ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስቷል፡፡ ስፖርት አብሮነት እና ወዳጅነትን የሚያሳድግ ዘርፍ በመኾኑ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ከአካባቢው ወጣቶች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፉን ተናግሯል፡፡
በቀጣይም መጭው የክረምት ጊዜ በመኾኑ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስፋት እና በማጠናከር ለማካሄድ መታቀዱ ተመላክቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን