የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በ9ኛው የመላው አማራ ጨዋታዎች የተሳተፉ የስፖርት ልዑክ አባላትን ሸለመ፡፡

0
78

በዘጠነኛው የመላው አማራ ጨዋታዎች ደብረ ብርሃንን ከተማ አስተዳደርን ወክለው 154 ስፖርተኞች በስምንት የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈዋል። የስፖርት ልዑካኑ 15 የወርቅ፣ 17 የብር እና 15 የነሐስ በድምሩ 47 ሜዳልያ በማስመዝገብ በኦሎምፒክ ስፖርቶች ከክልሉ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አውራሪስ አረጋ እንዳሉት በውስን ስፖርተኞች ከ18 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ስድስተኛ መውጣት መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው።

ውድድሩን ተከትሎ ስድስት ታዳጊዎች ወደ ጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል እንዲቀላቀሉ ተመልምለዋል ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ክልሉን ወክለው በሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ተለይተዋል ነው ያሉት።

በቀጣይ ስፖርቱን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። በውስን ስፖርተኞች እና በጀት ተሳትፎ ውጤታማ ከመኾን ባለፈ ስፖርተኞች የከተማዋ አምባሳደሮች መኾናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናግረዋል።

በቀጣይ የስፖርት መሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ብቁ እና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በስፖርት ዘርፉ ትብብር ላደረጉ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል። አልማ ስፖርቱን እንደ አንድ የትኩረት ማዕከል አድርጎ በማገዙ አቶ በድሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here