የጣና ሞገዶቹ ዛሬ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

0
106

ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ33ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሕር ዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል። በደረጃ ሠንጠረዡ በ48 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ መሪው መድንን ካሸነፉ በኋላ ውጤት ርቋቸዋል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት አቻ እና ሁለት ሽንፈቶች ገጥመቸዋል። ይህም የዋንጫ ተፎካካሪነታቸውን ላይ ጥያቄ እንዲነሳባቸው አድርጓል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። የአጥቂው ክፍልም ቢኾን ከዚህ በፊት በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ቢኾንም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ግን አንድ ግብ ብቻ ነው ያስቆጠረው። ይህ ቡድኑ በማጥቃትም በመከላከልም መድከሙን ያሳያል።

አዳማ ከተማ ይህን ጨዋታ ማሸነፉ የደረጃ ማሻሻል ያስገኝለታል። ቡድኑ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ነው። ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማስመዝገቡ ለዚህ ጨዋታ በሞራል እንደሚያግዘውም ይጠበቃል። ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ በኩል በጉዳት ምክንያት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ፣ መሳይ አገኘሁ፣ ግርማ ዲሳሳ እና አምሳሉ ጥላሁን አይሰለፉም። ወንድሜነህ ደረጄ ደግሞ በቅጣት ቡድኑን አያገለግልም።

ባሕር ዳር እና አዳማ ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ ተገናኝተዋል። የጣና ሞገዶቹ ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ ሦስት ጊዜ ድል አድርጓል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታውም ቀን 9፡00 ላይ ይካሄዳል። አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ምሽት 12፡00 የሚካሄድ የዛሬ ሌላኛው ጨዋታ ነው።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here