ማንቸስተር ሲቲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል።

0
120

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከበርንማውዝ ጋር በሚያደርገው የዛሬው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ ሽንፈትን ካስተናገደ የሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ተስፋው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ሲቲዎች በቅርቡ በኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ሽንፈት አስተናግደው የነበረ ሲኾን አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ለዚህ ጨዋታ በተጨዋቾች ስብስብ ላይ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

በተለይም የመጀመሪያ ምርጫቸው የኾነው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ወደ ቡድኑ ሊመለስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። አማካዩ ማቲዮ ኮቫቺች በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲኾን ወጣቱ ክላውዲዮ ኢቼቬሪ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ሊያደርግ ይችላል። በሌላ በኩል በርንማውዝ ይህንን ጨዋታ በድል ካጠናቀቀ በደረጃ ሰንጠረዡ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ድረስ ከፍ ማለት ይችላል። ይህ ደግሞ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ቦታ የማግኘት የሩቅ ህልማቸውን እውን ሊያደርግ ይችላል።

በርንማውዝ በቅርብ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ጥሩ ብቃት እያሳየ የሚገኝ ሲኾን ካለፉት 12 የፕሪምየር ሊግ ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ አስተናግዷል። ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከበርንማውዝ ጋር ባደረጋቸው ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሁሉን አሸንፏል። ሆኖም በርንማውዝ በኅዳር ወር በተደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ሲቲን 2ለ1 ማሸነፉ ለዚህ ጨዋታ የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።

ሲቲዎች ከጥቅምት 2022 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ በሁለት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ የቀሩ ሲኾን ይህ አዝማሚያ ከቀጠለ የውድድር ዘመኑ ፈታኝ ሊኾንባቸው ይችላል። በሌላ በኩል በርንማውዝ በዚህ የውድድር ዓመት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ኳስን በመንጠቅ ወደ ጎል ለመቀየር ያደረገው ሙከራ ከማንኛውም ቡድን የላቀ መኾኑ የሲቲን የተከላካይ መስመር ፈተና ላይ ሊጥል ይችላል።

በተለይም ኤቫኒልሰን በቅርብ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች ለበርንማውዝ የድል ተስፋን ሊያጠነክሩ ይችላሉ። በአጠቃላይ ይህ ጨዋታ ለማንቸስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ወሳኝ ሲኾን ለበርንማውዝ ደግሞ የአውሮፓ መድረክን የማግኘት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድል ነው።
ጨዋታውም ምሽት 4፡00 ይከናወናል።

በተመሳሳይ ሰዓት ዛሬ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ ከወልቭስ የሚያደርጉት ጨዋታም ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ ነው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here