ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬም ሲቀጥል ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ባሕር ዳር ከተማ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ይጠበቃል። በሊጉ ደረጃ በስድስት ነጥቦች የሚለያዩት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
ባሕር ዳር ከተማ 47 ነጥቦችን በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የጣና ሞገዶቹ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያላቸውን የ13 ነጥብ ልዩነት ለማጥበብም የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል። የጣና ሞገዶቹ ከሲዳማ ቡና ጋር በደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን አሸንፈው በመጨረሻው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ መጋራታቸው ይታወሳል። ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን አስቆጥረዋል።
መቻል 41 ነጥቦችን ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ከመሪዎቹ ጋር ያለው ልዩነት ሰፍቷል። ሁለቱ ቡድኖች ከአሁን በፊት ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተዋል። እያንዳንዳቸው ሦስት ጨዋታዎችን አሸንፈዋል፤ ሦስት ጨዋታዎችን ደግሞ በአቻ ውጤት ነው ያጠናቀቁት።
በእነዚህ ጨዋታዎች ባሕር ዳር ከነማ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር መቻል 11 ግቦችን አስቆጥሯል። የዛሬው ጨዋታው ቀን 9፡00 ላይ ይደረጋል። በሌላ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ከስሁል ሽረ ምሽት 12፡00 ይጫወታሉ።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን