የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት እየጣረ ያለው ቼልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።

0
149

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቼልሲ በሜዳው ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በጉጉት እየተጠበቀ ነው ባለፉት 14 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ቼልሲ አንድ ጊዜ ብቻ ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፉ እንዲኹም ማንቸስተር ዩናይትድ በስታንፎርድ ብሪጅ ካደረጋቸው 11 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፉ ጨዋታውን የበለጠ ተጠባቂ አድርጎታል።

በፕሪምየር ሊግ ታሪክ በሁለቱ ቡድኖች መካከል 27 ጊዜ የአቻ ውጤት የተመዘገበ ሲኾን የዚህ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታ በኦልድትራፎርድ 1ለ1 በኾነ ውጤት ተጠናቅቋል። ቼልሲ ያለፉትን 22 የሜዳ ላይ የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎችን ሳይሸነፍ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ካለፉት አምስት የሜዳ ውጭ የመጨረሻ ጨዋታዎቹ በአራቱ አሸንፏል።

ይኹን እንጂ ማንቸስተር ዩናይትድ የመጨረሻ የሜዳ ውጭ ጨዋታው በለንደን ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ሲኾን ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አሸንፎ አያውቅም። በ2025 ቼልሲ በሜዳው ባደረጋቸው ዘጠኝ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ 23 ነጥብ እና ሰባት ግቦችን ያስተናገደ ቡድን ነው። በተቃራኒው ማንቸስተር ዩናይትድ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ባደረጋቸው ሰባት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ባለፈው የውድድር ዓመት በዚሁ ጨዋታ ሀትትሪክ መሥራት የቻለው ኮል ፓልመር ለቼልሲ በፕሪምየር ሊግ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን አስቆጥሯል። ዛሬስ ይህንኑ ይደግማል ወይስ የሚለው ሌላው የጨዋታው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። ብሩኖ ፈርናንዴስ ለዩናይትድ በሁሉም ውድድሮች 56 የግብ ተሳትፎ በማድረግ የዩናይትድ ቁልፍ ተጫዋች ነው።

ቸልሲ የዛሬውን ጨዋታ ውጤት አጥብቆ ይፈልገዋል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመኾን እየተፎካከረ ያለው የለንደኑ ክለብ ጨዋታውን ማሸነፍ ብቻ ተስፋውን ያለመልምለታል። በዩናይትድ በኩል መጥፎ የውድድር ዓመታቸውን ለመደበቅ የዩሮፓ ሊጉን ፍጻሜ እየጠበቁ ሲኾን በዛሬው ጨዋታም አሸንፈው መነሳሳትን ለመፍጠር ይፈልጋሉ።

ጨዋታው ምሽት 4:15 ይጀምራል።

በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ዛሬ ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ አስቶንቪላ ከቶትንሃም ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።

ጨዋታውም ምሽት 3፡30 የሚካሄድ ይኾናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here