ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባርሴሎና በኤስፓንዮል ሜዳ በተካሄደው የደርቢ ጨዋታ 2ለ0 በኾነ ውጤት በማሸነፍ የ2024/25 የላሊጋ ዋንጫን ማንሳቱን አረጋግጧል። የ17 ዓመቱ ታዳጊ ኮከብ ላሚን ያማል ግሩም ግብ ያስቆጠረ ሲኾን፣ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ፌርሚን ሎፔዝ ከያማል የተመቻቸለትን ኳስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።
ይህ ድል ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን በሰባት ነጥብ በልጦ የዋንጫ ባለቤት እንዲኾን አግዞታል። ይህ የላሊጋ ዋንጫ ለባርሴሎና በዚህ የውድድር ዓመት ሦስተኛው ዋንጫ ሲኾን ቀደም ሲል ኮፓ ዴል ሬይ እና የስፔን ሱፐር ካፕን አሸንፏል። አሠልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በመጀመሪያ የውድድር ዓመታቸው ሦስቱንም የሀገር ውስጥ ዋንጫዎች በማንሳት ትልቅ ስኬት አስመዝግበዋል።
ቡድናቸው በዚህ የውድድር ዓመት በአራቱም የኤል ክላሲኮ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድን አሸንፏል። ባርሴሎና በሁሉም ውድድሮች 169 ግቦችን በማስቆጠር አስፈሪ የፊት መስመር እንዳለውም አሳይቷል። ባርሴሎና እሑድ ከቪላሪያል ጋር በሚደረገው የሜዳው ጨዋታ ዋንጫውን ተረክቦ ድሉን ከደጋፊዎቹ ጋር ያጣጥማል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን