የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ሽኝት ተደረገለት።

0
88

ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ሀገራት የሚሰባሰቡበት የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ዋንጫ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኳታር ዶሀ የምትወከልበትን ብሔራዊ ቡድን ሽኝት አድርጋለች። ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫው በአራት ሴት እና አንድ ወንድ ተወክላ በሻምፒዮናው ትሳተፋለች።

የዓለም ዋንጫው ከግንቦት ከ8 እስከ 16/2017 ዓ.ም በኳታር ዶሀ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ ብሔራዊ ቡድኑ ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ ዝግጅት እንዳደረገ በመግለጽ የሀገርን ክብር እና ዝና ከፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል። በምሥራቅ አፍሪካ ያለን የበላይነት በመጠቀም በኳታር በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከተሳትፎም በላይ ለውጤት በመትጋት ልምድ የሚወሰድበት ጭምር እንዲኾን ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅ አፍሪካ የበላይነቱን የሚያጠናክርበትን ሻምፒዮና በማዳጋስካር ያካሄዳል። ብሔራዊ ቡድኑ በአምስት ሴት እና በአምስት ወንድ ተወክሎ ሻምፒዮናውን ሰኔ 3/2017 ዓ.ም በማዳጋስካር ያካሄዳል። የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የሥራ አሥፈፃሚ አባላት ብሔራዊ ቡድኑ በድል እንዲመለስ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ከሽኝቱ ጎን ለጎን በአፍሪካ ሻምፒዮና ውጤት ላስመዘገቡ እና ለተሳተፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርተኞች፣ አሠልጣኞች እና አባላት የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል። በሀገራችን የአፍሪካ ሻምፒዮና ከጥቅምት ከ2 እስከ 8/2017 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል። በዚህም ፌዴሬሽኑ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ እና የተሻለ ተሳትፎ ላደረጉ የቡድኑ አባላት ከ10 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here