ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጣሊያን ዋንጫ (ኮፓ ኢታሊያ) ኤሲሚላን እና ቦሎኛ ለዋንጫ ይፋለማሉ። ጨዋታው በሮም ኦሎምፒክ ስታዲየም ይደረጋል። የሁለቱ ቡድኖች ወቅታዊ ብቃት ሲታይ ኤሲ ሚላን በሁሉም የውድድር መድረኮች ባደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፎ አንድ አቻ ሲወጣ አንድ ጨዋታ ተሸንፏል።
በቅርቡ በሴሪኤ ቦሎኛን 3ለ1 ማሸነፋቸውም በዛሬው ጨዋታ የተሻለ መነሳሳት እንደማፈጥርላቸው ተገምቷል። በሌላ በኩል ቦሎኛ በአምስቱ የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎቻቸው ሁለት ጊዜ አሸንፈው ሁለት ጊዜ አቻ የወጡ ሲኾን አንድ ጊዜ ተሸንፈዋል። ምንም እንኳን በቅርቡ በሚላን ቢሸነፉም በጣሊያን ዋንጫ ጥሩ እንቅስቃሴ አድረገው ለዋንጫው ደርሰዋል።
በሁለቱ ቡድኖች የታሪክ ግንኙነት ኤሲ ሚላን የበላይነት አለው። ከተገናኙባቸው 50 ጨዋታዎች ውስጥ ሚላን 32 ጊዜ ሲያሸንፍ ቦሎኛ ሰባት ጊዜ ብቻ አሸንፏል። 11 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል።
በዚህ የውድድር ዘመን በጣሊያን ዋንጫ ኤሲ ሚላን 13 ግቦችን ሲያስቆጥር ቦሎኛ 10 አስቆጥሯል። ይህም ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት አቅም እንዳላቸው ያሳያል።
የዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖር ቢቢሲ በስፖርት ገጹ አስነብቧል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን