ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹን ዛሬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያገናኛል። በሊጉ ሠንጠረዥ 46 ነጥብ ይዞ ሦሥተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ባሕር ዳር ከተማ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይለዋል።
የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ተከታታይ ሦሥት ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን እያሸነፉ መምጣታቸው ጥሩ የኾነ የመንፈስ ጥንካሬ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። በተለይም ባለፈው ሳምንት ጨዋታ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድንን 2ለ1 ማሸነፍ የቻለው የባሕር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለማሸነፍ ብዙም ሊከብደው እንደማይችል ነው የሚጠበቀው።
ቡድኑ በፈጣን አጥቂዎች የሚመራ ጠንካራ የፊት መስመር ያለው መኾኑ ጨዋታውን በበላይነት ሊመራ ይችላል የሚል ቅድመ ግምት እንዲያገኝ አስችሎታል። በ37 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦሥት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ነው የሚጫዎተው። ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሽንፈት እና በአቻ የጨረሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጣና ሞገዶቹ ጋር ያለው ጨዋታ ፈታኝ እንደሚኾንበት ይገመታል።
ጥሩ የአጥቂ ሥፍራ ተጫዋቾች ያሉት ንግድ ባንክ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች 5 ግቦችን አስቆጥሯል። ይሁን እንጅ ቡድኑ በ5 ኳሶች መረቡ መደፈሩ የተከላካይ ክፍሉ ደካማ መኾኑን የሚያሳይ ነው። ይህን ድክመቱን አሻሽሎ የሚመጣ ካልኾነ የመሸነፍ ዕድሉ ሰፊ ይኾናል። ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሸር ካምፓኒ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ጨዋታው ቀን 9፡00 ይካሄዳል።
በሌላ የ29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መቻል ከሽረ እንዳሥላሴ 12፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሊጉን የኢትዮጵያ መድን በ57 ነጥብ ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና በ48 ነጥብ ሁለተኛ ነው፤ የጣና ሞገዶቹ በ46 ነጥብ ሦሥተኛ ደረጃን ይዘዋል። ባሕር ዳር ከተማ ይህን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ ከመሪው ጋር ያለውን ነጥብ ወደ 8 ዝቅ ከማድረጉም በላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን