ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በ17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ስሑል ሽረ እና በ37 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ወላይታ ድቻዎች 9፡00 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ለስሑል ሽረ ይህ ጨዋታ በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ተስፋ የሚያለመልም ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ምንም እንኳን በ17 ጨዋታዎች ያስቆጠሩት አንድ ጎል ብቻ ቢኾንም የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴያቸው ላይ መሻሻል ታይቷል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ አግኝተዋል።
በሌላ በኩል ወላይታ ድቻዎች በቅርብ ጊዜ በተከታታይ ሽንፈት ቢያጋጥማቸውም ከወራጅ ቀጣናው ቡድን ጋር የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሳኝ ነው። የአጥቂ ክፍሉ የተሻለ ቢመስልም የኋላ መስመራቸው በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ክፍተት ታይቶበታል።
በሁለቱ ቡድኖች መካከል ቀደም ሲል የተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች በሁለት አቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ወላይታ ድቻ አንድ ጊዜ አሸንፏል። በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ለየራሳቸው ግብ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ሌላው በወራጅ ቀጣናው የሚገኙት አዳማ ከተማ እና ወልዋሎ አድግራት 12፡00 የሚያካሂዱት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ድል የናፈቃቸው 16ኛ ደረጃ ላይ ያሉት አዳማዎች ከሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ወልዋሎን ይገጥማሉ። የኋላ መስመራቸው ደካማ ቢኾንም ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይፈልጋሉ። ቢኒያም አይተን ጉዳት ላይ ቢኾንም ቀሪው ቡድን ዝግጁ እንደኾነ ታውቋል።
በሌላ በኩል ወልዋሎ በሊጉ የመቆየቱ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። አንድ ጊዜ ብቻ ያሸነፉት ወልዋሎዎች ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከእያንዳንዱ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ይፈልጋሉ። የኋላ መስመራቸው አኹንም ደካማ ቢኾንም በዚህ ጨዋታ የሚቀር ተጨዋች የላቸውም። ቀደም ባሉት አምስት ጨዋታዎች አዳማ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ ወልዋሎ አንድ ጊዜ አሸንፏል። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን