አጥቂው ባርሳ ከአይነኬው ኢንተር-የሻምፒዮንስ ሊጉ ሌላ መልክ!

0
96

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት ለአርሰናል ያልተመቸው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬም ባርሴሎናን ከኢንተር ሚላን አፋጧል። ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሌሎች የላቁበት የየራሳቸው ጥንካሬ አላቸው። ባርሴሎና በሻምፒዮንስ ሊጉ በዚህ ዓመት እስካኹን 37 ግቦችን አስቆጥሯል። ይህም ከየትኛውም ቡድን የበለጠ ነው።

ኢንተር ሚላን በበኩሉ በተመሳሳይ በሻምፒዮንስ ሊጉ እስካኹን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ስምንት ጊዜ መረቡን አላስደፈረም። ይሄም ዘንድሮ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከተሳተፉ ቡድኖች ሁሉ የተሻለ መረቡን የጠበቀ ቡድን አድርጎታል። ስለዚህ የዛሬው ጨዋታ የተሻለ የሚያጠቃው ቡድን መረቡን ከማያስደፍረው ቡድን ጋር የሚያደርጉት ነው።

አውሮፓ መድረክ ባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን እስካኹን 16 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ከዚህ ውስጥ ባርሴሎና ግማሹን አሸንፈዋል። አምስት ጊዜ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፤ ሦስት ጊዜ ደግሞ ኢንተር ሚላን ድል አድርጓል። ኾኖም በቅርብ የሁለቱ ግንኙነት በ2022/23 የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ የጣሊያኑ ክለብ የበላይነት አለው። ከሜዳው ውጭ ሲያሸንፍ፣ በሜዳው ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

ይህ ባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ላይ የሚገናኙበት ሁለተኛው ጊዜ ሲኾን ሁለቱም ጊዜያት በግማሽ ፍፃሜው ላይ ነው መገናኘት የቻሉት። በ2009/10 ጆዜ ሞሪንሆ የሚመሩት ኢንተር ሚላን በድምር ውጤት 3ለ2 አሸንፎ ባርሴሎናን ከውድድር ውጭ ያደረገበት የቅርብ ትዝታ ነው።

ባርሴሎና በዚህ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ በሜዳው ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አላስተናገደም፤ አምስት ጊዜ በአሸናፊነት ተወጥቷል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ባርሴሎና በሃንሲ ፍሊክ ስር በአማካይ በሻምፒዮንስ ሊግ 3 ነጥብ 1 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ክለብ ሲኾን ይህም ሁለተኛው ከፍተኛው ኾኖ ተመዝግቧል። ከዚህ በፊት የሃንሲ ፍሊኩ ባየርን ሙኒክ 3 ነጥብ 2 ጎቦችን በአማካይ በማስቆጠር ቀዳሚው ነው።

የኢንተር ሚላኑ አሠልጣኝ ሲሞን ኢንዛጊ የዛሬው ጨዋታ 50ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታቸው ነው። ይህንንም ማሳካት የቻሉ ሰባተኛው ጣሊያናዊ አሠልጣኝ ብሎ ታሪክ ይጽፋቸዋል። ላውታሮ ማርቲኔዝ በሻምፒዮንስ ሊግ ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ለኢንተር ሚላን ግብ አስቆጥሯል። በዚህ ጨዋታ ላይም ግብ ካስቆጠረ ከኤዲንሰን ካቫኒ በመቀጠል በውድድሩ በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛው ደቡብ አሜሪካዊ ተጫዋች ይኾናል።

የባርሴሎናው ራፊንሃ በዚህ የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዘመን ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ነው። ለቡድኑ ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር እና ለአጋሮቹ አመቻችቶ በመስጠት ለካታሎኑ ክለብ ሁነኛ ኾኗል። በዛሬው ተጠባቂ ጨዋታም በባርሴሎና በኩል ራፊንሃ እና ያማል፣ በኢንተር በኩል ደግሞ ላውታሮ ይጠበቃሉ። ባርሴሎናዎች ሮበርት ሉዋንዶስኪን በጉዳት አያሰልፉም።

ጨዋታውም ምሽት 4፡00 ሰዓት ይካሄዳል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here