የሜዳ ላይ ፈርጦችን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት

0
124

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእግር ኳሱ ሜዳ ላይ ፈርጥ ናቸው። ጨዋታ እንዳይበላሽም ኾነ ግለቱን ጠብቆ ለማቆየት እንደቅመም ኾነው ያገለግላሉ የእግር ኳስ ዳኞች። ዓለም ላይ ተጠባቂ ጨዋታዎች ሳይበላሹ እንዲያልቁ የእነዚሁ ቅመሞች ሚና ትልቅ ነው። በጨዋታ እንደወርቅ ነጥሮ የወጣው ቡድን ብቻ ዋንጫ እንዲያነሳ ያላቸው ሚናም ከፍ ያለ በመኾኑ ወሳኝ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች በባትሪ ተፈልገው ጨዋታ ይመራሉ።

በዓለም ላይ ጨዋታዎችን የሚመሩ፣ ኢትዮጵያን በማስጠራት አምባሳደርም የሚኾኑ ድንቅ ዳኞች እንደሀገር ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። አማራ ክልልም እንደ ሀገርም ኾነ በዓለምአቀፍ ደረጃ በብቃት የሚሳተፉ እንደ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለ ኢየሱስ ባዘዘው ያሉ ዕውቅ እና በሙያቸው አንቱ የተባሉ ዳኞችን ያፈራ ክልል ነው።

አማራ ክልል ያፈራቸው እውቅ ዳኞች እንዳሉ ኾነው ቀጣይ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትም ይጠበቅበታል። ከዚህ አኳያ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የዳኝነት የሙያ ሥልጠናዎችን እየሰጠም ይገኛል፡፡ በአማራ ክልል የእግር ኳስ ዳኞችን ከታች ጀምሮ በማሠልጠን ብቁ ለማድረግ የተለያዩ የዳኝነት ሥልጠናዎች መስጠቱን የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርሃኔ ጌትነት ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በአሠልጣኝነት እና በዳኝነት ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ሥልጠናው ከመጀመሪያ ደረጃ ዳኝነት ጀምሮ ሁለተኛ ደረጃ እያለ እና እያደገ የሚሰጥ ሥልጠና ነው፡፡ በክልሉ በርካታ የእግር ኳስ ዳኞች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው በየሁለት ዓመቱ ደግሞ የደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ2017 ዓ.ም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የተለያዩ የዳኝነት የሙያ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል። በዚህም 175 ዳኞች የተለያየ ደረጃ ያላቸው የዳኝነት ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ከነዚህ ውስጥ 13ቱ ሴት ዳኞች ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ ይሠለጥናሉ ተብለው ከተያዙ ዕቅዶች አንጻር የሚቀሩ ሥልጠናዎች አሉ ያሉት የጽሕፈት ቤት ኀላፊው በቀሪ ወራቶች አሠልጥኖ ብቁ ለማድረግ ጥረቶች መቀጠላቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here