የሌስስተር ሲቲ የምንጊዜውም ምርጡ ተጫዋች፦

0
127

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእግር ኳስ ከማይረሱ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው ይሉታል። በሳል፣ ነገር አዋቂ እና አርቆ የሚያስብ እንደኾነም ይነገርለታል ጃሚ ሪቻርድ ቫርዲን። በእግር ኳስ ያን ያክል ስማቸው በማይታወቁ ክለቦች የተጫወተው ቫርዲ፣ ከዝቅታ ተነስቶ የከፍታ ታሪክ ጽፏል።

የታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ጃሚ ቫርዲ በእንግሊዝ የእግር ኳስ ውስጥ በሌስተር ሲቲ የፊት መስመር ተጫዋችነት ከመታወቁ አስቀድሞ በትንንሽ ክለቦች ተጫውቷል። ጃሚ ቫርዲ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ጥር 11/1987 በሸፊልድ እንግሊዝ ውስጥ ነበር የተወለደው። ከሰፈር እስከ ትምህርት ቤት እግርኳስን የሚያንጠባጥበው ጃሚ ቫርዲ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ደክሟል።

ሩቅ አሳቢው ይህ እውቅ ሰው የወደፊት መዳረሻውን ለመወሰን ጠንክሮ ይሠራ ነበር። አንድ ነገር ለማሳካት ስትነሳ ብዙ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ተስፋ አስቆራጭ ጉዳዮች ቢኖሩም ብዙም ትኩረት ሳትሰጥ ግን ደግሞ እንዳያሰናክሉህ እያሰብክ ወደ ፊት ተራመድ የሚለው ይህ እውቅ የእግር ኳስ ተጫዋች እሱም እሳቤውን በተግባር ፈጽሞታል።

ስሙ ወደ ገነነበት ሌስስተር ሲቲ ከመግባቱ አስቀድሞ ፊልትውድ ታውን እና ሃይሊፋክስ ታውን ለተባሉ ትንንሽ ክለቦች ተጫውቷል። በእነዚህ ክለቦች ያሳየው ብቃት በ2012 ወደ ሌስስተር ሲቲ እንዲዛወር ምክንያት ኾነውታል። የሌስስተር ሲቲ ቆይታው የቫርዲ ሕልም እንዲወጣ ምክንያት ኾነ። ክለቡ በ2013/14 የቻምፒዮንሺፕ ዋንጫን በማንሳት ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

በፕሪሚየር ሊጉም አስደናቂ ብቃቱን በሚገባ አሳይቶ ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ ማጻፍ የቻለ ጠንካራ ሰው ለመኾንም በቅቷል። ጄሚ ቫርዲ በ2015/16 የውድድር ዘመን ሌስስተር ሲቲ ያልተጠበቀውን የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ባነሳበት የማይረሳ የውድድር ዘመን ላይ የተጫወተው ሚና ምንግዜም በክለቡ እና በአድናቂዎቹ እንዳይረሳ አድርገውታል። በውድድር ዘመኑም 24 ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑ ዋንጫውን እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጃሚ ቫርዲ በዚህ ድል ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲኾን በተከታታይ 11 ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠር አዲስ ክብረ ወሰን መያዝ ችሏል። በሊጉ ውስጥ በተከታታይ በርካታ ግቦችም በማስቆጠር ለሌስስተር ሲቲ ቁልፍ ተጫዋች መኾን የቻለ ነው። ጃሚ ቫርዲ በፍጥነቱ፣ ኳስን በመከተል ብቃቱ እና በአጨራረሱ የታወቀ እና ብዙዎች የሚያደንቁትም ተጫዋች ነው። በተለይም የተከላካይ ተጫዋቾችን ጀርባ በመጠቀም ኳስን ወደ ጎል በመቀየር የተዋጣለት ነው።

በተጨማሪም የአየር ላይ ኳሶችን በመግጨት እና የፍጹም ቅጣት ምቶችን በመጠቀም ጎል ማስቆጠር ያውቅበታል። የጨዋታ ስልቱ ተጋጣሚን ሁልጊዜ በጭንቀት ውስጥ የሚጥል እና የማያቋርጥ እንቅስቃሴን የሚፈልግ ነው። ቫርዲ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም ተጫውቷል። በዩሮ 2016 እና በ2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲኾን ወሳኝ የሚባሉ ግቦችንም ማስቆጠር ችሎ ነበር።

ፈጣኑ ተጨዋቾች የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ የወርቅ ጫማን 2019/20 የውድድር ዘመን ላይ በ23 ግቦች መውሰድም ችሏል። 2015/16 የውድድር ዘመን ላይ የእግር ኳስ ጸሐፊዎች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች መባል የቻለ ነው። በሌስስተር ሲቲ በርካታ የወሩ ምርጥ ተጫዋች ሽልማቶችንም አግኝቷል።

ጄሚ ቫርዲ በሜዳ ላይ ካስመዘገባቸው ስኬቶች ባሻገር ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመፍታት ላይም ያለው ተሳትፎ የሚያስደንቀው ነው። ከእዚህ ተግባሩ መካከል እሱ እና ባለቤቱ ርብቃህ ቫርዲ ችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናትን እና ወጣቶችን ለመደገፍ በማሰብ ያቋቋሙት የቫርዲ ፋውንዴሽን ይጠቀሳል።

ይህ ፋውንዴሽን በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበረሰብ ልማት ሰፊ ሥራ እንዲሠራ ታሳቢ አድርገው ያቋቋሙት ተቋም ነው። ሕጻናት ላይ መሥራት የነገን ትውልድ መበየን እንጀኾነ የሚያስበው ጄሚ ቫርዲ ይህንንም እሳቤውን ወደ ተግባር እየቀየረ ያለ የመልካም ልብ ባለቤት ነው።

ጃሚ ቫርዲ ከሚታወቅባቸው ሌሎች ሥራዎቹ ውስጥም የጸረ ዘረኝነት ትግል አንዱ ነው። ቫርዲ በእግር ኳስ እና በኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ጽንፈኝነትን የሚዋጋ እና የሚጠላ የእግር ኳስ ሰው ነው። ተጫዋቹ አድሏዊ ባሕሪያትን በመቃወም ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያስተጋባ ከመኾኑም በላይ የእኩልነት መርኾዎችን በሚያራምዱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት በመሳተፍም ይታወቃል።

የአዕምሮ ጤና ግንዛቤ ፈጠራ ላይ ሰፊ ተሳትፎ እንደሚያደርግ የሚነገርለት ጃሚ ቫርዲ የአዕምሮ ደኅንነትን መፍትሔ የመስጠት አስፈላጊነትን በመገንዘብ ለአዕምሮ ጤና ግንዛቤ ድጋፉን አሳይቷል። በሌስስተር ሲቲ 13 አስደናቂ ዓመታትን ያሳለፈው ቫርዲ በዓመቱ መጨረሻ ከክለቡ ጋር እንደሚለያይ ታውቋል።

ለዓመታት ለሌስስተር ሲቲ ታምኖ ተጫውቷል። በብቃቱ ጣሪያ ላይ እያለ ከኪንግ ፓወር እናስኮብልልህ ያሉትን ቡድኖች ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ ኖሯል። ሌስስተር ሲቲ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ነው ብሎ ታምኗል። የማይታመን የሚመስለውን የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫ ሲያሸንፉ አብረውት የነበሩት ከዋክብት ሌስስተር ሲቲን ለቅቀው ወደሌላ ክለብ ሲያመሩ ቫርዲ ግን በዛው ቀርቷል። የቡድኑ አምበል ኾኖም መርቷል።

በዚህ የውድድር ዘመን መጨረሻ ከሌስስተር ሲቲ ጋር እንደሚለያይ ሲታወቅ ” ይህ ቀን ውሎ አድሮ እንደሚመጣ አውቅ ነበር። በዚህ ክለብ 13 የማይታመኑ ዓመታትን አሳልፌያለሁ። ብዙ ስኬት እና አንዳንድ ውድቀቶች አይቻለሁ። ሌስስተር ሁሌም በልቤ ውስጥ ቦታ ይኖረዋል” ብሏል።

በአንድ ሚሊዮን ፓውንድ ፊልትውድ ታውን ሌስስተር ሲቲን የተቀላቀለው ቫርዲ የፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ፣ ኤፍኤ ካፕ ፣ ሁለት ሻምፒዮንሺፕ እና ኮሚኒቲሺልድ ዋንጫዎችን አሸንፏል። ሌስስተር ሲቲ ዋንጫ ካሸነፈበት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ሲወርድ ቫርዲም አብሮ ወርዶ ተጨዋቷል። በከፍታም በዝቅታም ዘመን ለክለቡ ታምኗል።

ሌስስተር ሲቲ ቫርዲ ከክለቡ እንደሚለቅ ከታወቀ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት “አንተ የክለቡ የምንጊዜምም ምርጡ ተጨዋች ነህ” ብሎታል።

የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ደግሞ ቫርዲ በሌስስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ የነበረውን ዘመን በዚህ ውድድር መጨረሻ እንደሚቋጭ ገልጿል። የቫርዲ ከሌስስተር ሲቲ ጋር መለያየት በ2015/16 ዋንጫ ካሸነፈው ቡድናቸው የሚቀር ተጫዋቾች አይኖርም ማለት ነው ብሏል።

በዚህ የውድድር ዓመት መጨረሻ ከሌስስተር ሲቲ ጋር የሚለያየው የ38 ዓመቱ ቫርዲ እግር ኳስ በቃኝ ይላል ወይስ ወደ ሌላ ክለብ አቅንቶ ይጫወታል? የሚለው ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here