ለሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ የሚደረገው ትንቅንቅ፦

0
122

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ውድድሩን ሊያጠናቅቅ አምስት ጨዋታዎች ይቀሩታል። ሊቨርፑል ዋንጫውን ለማንሳት ጫፍ ደርሷል። ከታች ወራጅ ክለቦችም ቀድመው እየተለዩ ነው። ሳውዝአፕተን እና ሌስተር መውረዳቸው ተረጋግጧል። ኢፕሲች ታውንም በሂሳብ ደረጃ ገና አለመረጋገጡ ካልኾነ በቀር ከሊጉ የመትረፉ እድሉ የጠበበ ነው።

ከወትሮው በተለየ ለዋንጫ እና ላለመውረድ የሚደረገው ትግል እንዲህ የተቀዛቀዘበት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በአውሮፓ ውድድሮች የሚያሳትፍን ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ትንቅንቅ ግን አጓጊ ነው።

በተለይ በቀጣይ ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚደረገው ፉክክር አምስት ክለቦች በሦስት ነጥብ ብቻ ተለያይተው መቀመጣቸው ቀጣይ ጨዋታዎችን ተጠባቂ አድርጓል።

እንግሊዝ በ2025/26 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በአምስት ክለቦች ትወከላለች።

ይህን ቦታ ለማግኘት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኖቲንግሃም ፎረስት ጀምሮ ሰባተኛ ላይ እስካለው አስቶን ቪላ አምስት ክለቦች እድሉ አላቸው። በኖቲንግሃም እና አስቶንቪላ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነትም ሦስት ብቻ ነው።

ከሊቨርፑል እና አርሰናል በመቀጠል ኖቲንግሃም፣ ኒውካስትል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ቼልሲ እና አስቶንቪላ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል። በቀጣይ አምስት ጨዋታዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦችም የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታቸውን ያረጋግጣሉ።

ከወትሮው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፍ ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ መድረኮች ባሳዩት ውጤታማነት ተጨማሪ አንድ ክለብ በሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሳተፍ እድል ተሰጥቷል።

በዩሮፓ ሊግ ዋንጫን የእንግሊዝ ክለብ የሚያሸንፍ ከኾነ ደግሞ እንግሊዝ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በስድስት ክለቦች የመወከል እድል ይኖራታል። በዩሮፓ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሀም ሆትስፐርስ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል።

በተመሳሳይ በዩሮፓ ሊግ እና ኮንፍረንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚደረገው ትግልም የፕሪምዬር ሊጉ ውበት ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here