የፕሪምየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

0
99

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቅርብ ጨዋታዎች ጥሩ ያልኾነ ውጤት እያስመዘገበ ነው። በአንጻሩ ኢትዮጵያ መድን በአሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እየተመራ በሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ምንም እንኳን በቅርብ ጨዋታዎች የተወሰነ የግብ እጥረት ቢታይባቸውም በአጠቃላይ የቡድኑ አቋም ጠንካራ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ግንኙነታቸው ኤሌክትሪክ 16 ጊዜ በማሸነፍ ሲመራ መድን ሰባት ጊዜ አሸንፏል። ጨዋታውም ቀን 9:00 ይካሄዳል። በሌላ የዛሬ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት እየተጣጣሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በቅርቡ ባሳዩት መሻሻል ንግድ ባንክን ለመፈተን ዝግጁ ኾነዋል።

በሌላ በኩል ንግድ ባንክ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ለመውጣት እና የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ለማረጋገጥ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይፈልጋል። ሀዋሳ ከተማ በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እየተመራ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱን በማሻሻል የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ነው። ንግድ ባንክም በቅርብ ጨዋታዎች የተሻለ ቢኾንም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና በተከላካይ የሚታዩ ድክመቶችን በማረም የተሻለ መኾን ይጠበቅበታል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረጉ 38 ጨዋታዎች ንግድ ባንክ በ15 ሲያሸንፍ ሀዋሳ ከተማ 10 ጊዜ አሸንፏል። ጨዋታውም ምሽት 12:00 ይካሄዳል። ሊጉን ኢትዮጵያ መድን በ48 ነጥብ ሲመራ ባሕር ዳር ከተማ በ40 ነጥብ ይከተላል። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በ39 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here