ባሕር ዳር:ሚያዝያ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ባሕርዳር ከተማን ከመቐለ 70 እንደርታ የሚያገናኘው ጠንካራ ጨዋታ ደግሞ 12:00 ይደረጋል።
በ37 ነጥብ ሦስኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ በሲዳማ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም አስበው ይጫወታሉ።
በ28 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ያሉት መቐለ 70 እንደርታዎችም ከወራጅ ቀጣናው ለመራቅ በማሰብ የዛሬው ጨዋታ ያደርጋሉ።
ቀን 9፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ ነው።
ፋሲል ከነማ ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና አንድ ለባዶ ቢሸነፍም ወደ ቀድሞ ብቃቱ ለመመለስ እና በደረጃ ሰንጠረዡ የተሻለ ቦታ ለመያዝ ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል።
ቡድኑ በቅርብ ጨዋታዎቹ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ መሻሻል አሳይቷል። ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ ሽንፈት ቢስተናግዱም ያሳዩት እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። ዛሬ ድል ካገኙ በደረጃ ሰንጠረዡ ቢያንስ ሁለት ደረጃዎችን የማሻሻል ዕድል አላቸው።
በ26 ነጥብ በ14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዎችም ከስጋት ቀጣናው ገና ባልራቁበት ኹኔታ የሚገኙ በመኾኑ በዛሬው ጨዋታ ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካኹን 15 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም ቡድኖች ስድስት ጊዜ አሸንፈዋል፤ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን