ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ”ለ” ላይ የተደለደሉት ደሴ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሊጠናቀቅ ሁለት ሣምንታት በቀሩት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ን እየመራ የሚገኘው ነገሌ አርሲ እና በሁለተኛነት የሚከተለው የአማራ ክልል ተወካዩ ደሴ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ከሁለቱ ቡድኖች ባለፈ ተጋጣሚዎቻቸውም ላለመውረድ ስለሚጫወቱ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
በነገሌ አርሲ እና ደሴ ከተማ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ሁለት ብቻ መኾኑ ፉክክሩን ልብ አንጠልጣይ አድርጎታል። በዛሬው 21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ ከስልጤ ወራቤ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታል፡፡ ደሴ ከተማ ደግሞ ከየካ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተመሳሳይ 5 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
የደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ዳዊት ታደለ ለአሚኮ እንደገለጹት የደሴ ተጋጣሚ የካ ክፍለ ከተማም ኾነ ነገሌ አርሲን የሚገጥመው ስልጤ ወራቤ ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ ይጫወታሉ ብለዋል፡፡ ጨዋታው የቡድኖቹን ሕልውና የማስቀጠል በመኾኑ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ነው ያሉት፡፡
የደሴ ከተማ ቡድን ከበፊቱ ጨዋታዎች በብዙ መንገድ ተሻሽሏል ያሉት አሠልጣኝ ዳዊት ተጫዋቾቹ የነበረባቸውን አብዝቶ የመጨነቅ የስነ ልቦና ችግር ተወግዶ በቴክኒክ እና ታክቲክ ረገድም በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የደሴ ቡድን ማሸነፍ እንዳለ ኾኖ ነገሌ አርሲ ከተሸነፈ ወይም አቻ ከተለያየ ደሴ ከተማ የምድቡን መሪነት እንደሚረከብ አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎችም ደሴ ከተማ ዋጋ ከፍሎ ለውጤት ይጫወታል ብለዋል፡፡
የቡድኑ ደጋፊዎች ውጤት ሲገኝም ኾነ ሲጠፋ ይደግፉናል ያሉት አሠልጣኝ ዳዊት አሁንም ያለተስፋ መቁረጥ በትዕግስት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የደጋፊዎች ፍላጎታት ተሳክቶ ደስታቸውን ከማየት በላይ ደስታ የለኝም ያሉት አሠልጣኙ በሚቻለው መንግድ ሁሉ የደሴ ከተማን ቡድን ወደ ከፍታ ለማምጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!